ዱከም፡- ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረውን ክስተት ተከትሎ በዱከም ከተማ የተፈጸመው ድርጊት የከተማው ነዋሪም ሆነ የኦሮሞ ህዝብ ራሱን እንዲፈትሽ፣ አንድነቱን አጠናክሮም ለጋራ ልማት እንዲሰራ ማንቂያ ሊሆነው እንደሚገባ አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ ዱከም የሰላም አምባሳደር የሆነች ከተማ ናት። ሰሞኑን በክልሉ የነበረውን ተቃውሞ ተከትሎ በከተማዋ የተፈጠረው ችግርም የከተማዋን ህዝብና ወጣት የማይወክል፤ ይልቁንም ራሱን እንዲፈትሽ፣ ለጋራ ሰላምና ልማቱ በንቃት እንዲሰራ ሊያነቃው የሚገባ ተግባር ነው።
ወጣት ሌሊሳ ጫልቺሳ፣ በከተማዋ መልካ ዱከም ቀበሌ ነዋሪ ነው። ወጣቱ እንደሚለው፤ የከተማዋ ህዝብ በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር ያለበት ቢሆንም በዚህ መልኩ የከተማዋን ስዕል በሚያጎድፍ፣ ሰላሙንም አደጋ ላይ የሚጥልና ንብረትን የሚጎዳ ተግባር ላይ ተሰማርቶ አያውቅም። አሁን የተፈጠረውም የከተማው ህዝብም ሆነ ወጣት ተግባር ካለመሆኑም በላይ ሕብረተሰቡ ራሱን በአግባቡ እንዲፈትሽ በቀጣይም ለመሰል ተግባር ከሚያነሳሱት ሃይሎች ራሱን ጠብቆ ለሰላምና ልማቱ በጋራ መቆም እንዳለበት ትምህርት የሰጠ ነው።
ሁነቱ ሁለት እውነቶችን ያሳየ መሆኑን የሚናገረው ወጣት ሌሊሳ፤ አንደኛ የኦሮሞ ህዝብ ዛሬም አንድነትና ሰላሙን የሚፈትኑ ሃይሎች መኖራቸው በግልጽ የታየበት ሲሆን፤ ሁለተኛ የኦሮሞ ህዝብ በውስጡ በአካባቢና ዞን የመከፋፈል አዝማሚያ መያዙ ገሀድ የወጣበት መሆኑን ይገልጻል።
በሰሞኑ የተፈጠረው ችግርም ይሄንኑ በውስጡ ያለን መከፋፈል ተጠቅመው አንድነትና ሰላሙን የማይፈልጉ ሃይሎች ያከናወኑት ሲሆን፤ ችግሩን ለማባባስም የብሔርና የሃይማኖት ገጽታን እንዲላበስ ጥረት የተደረገበት መሆኑን ወጣት ሌሊሳ ተናግሯል።
በሰላም ወዳዱ የከተማዋ ነዋሪና ወጣት እንዲሁም በጸጥታ ሃይሉ ቅንጅት ሊገታ መቻሉን በመጠቆም፤ አሁንም የከተማዋን ሰላም፣ የህዝቡን አንድነትና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ወጣቱ፣ ህዝቡ፣ የጸጥታ ሃይሉና መንግስት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስቧል።
ከተማዋ ታሪካዊ፣ የኦዳ ነቤ እና የቱለማ ኦሮሞ መገኛ መሆኗን የሚናገሩት የጠዴቻ ቀበሌ ነዋሪ አቶ በሪሁን ቤኛ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የተፈጠረው ችግር ድንገት የተፈጠረና በከተማዋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ጫና ፈጥሮ የቆየ እንደነበር ይገልጻሉ።
በሰላማዊ መንገድ ተጀምሮ በሂደት በተፈጠረ የሃሳብ ልዩነት ወደግጭት ያመራው ክስተትም በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ መሆኑን በመጠቆም፤ ሂደቱ በህዝቡና በጸጥታ ሃይሉ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሊገታ መቻሉን ተናግረዋል።
የከተማው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ በለጠች ኃይለሚካኤል በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ክስተቱ በሰው ህይወት ላይ ያስከተለው ጉዳት ባይኖርም የአካልና የንብረት ጉዳት ደርሷል።
ህዝቡ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች ከጸጥታ አካሉ ጋር ሆነው የሚያስመሰግናቸውን የማረጋጋት ስራ ባይሰሩ ኖሮ ከዚህ በላይ አደጋ ይደርስ ነበር ያሉት ወይዘሮ በለጠች አሁን ላይ ከተማዋ መረጋጋቷንና ተጠርጣሪዎችን ለህግ የማቅረብ ስራውም ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2012
ወንድወሰን ሽመልስ