አዲስ አበባ፡- በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከነበረው የተሻለ የስራ እድል ለመፍጠር በያዝነው በጀት አመት አምስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተጠናቀው ወደ ስራ እንደሚገቡ ተጠቆመ።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ደርቤ ደበሌ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት ኮርፖሬሽኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከማስፋፋት ጎን ለጎን በዘርፉ ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር እየሰራ ነው።
አቶ ደርቤ እንደሚናገሩት በአገሪቱ እስካሁን 12 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሰባቱ ወደ ስራ ገብተዋል፤ ምርቶቻቸውንም ለውጪ ገበያ ማቅረብ ጀምረዋል። ቀሪዎቹ አምስቱ ደግሞ በዚህ አመት ተጠናቅቀው ወደ ስራ ይገባሉ።
እስካሁን በዘርፉ በተከናወኑት ተግባራት ምክንያት በርካታ የስራ እድሎች ተፈጥረው ዜጎችን የእድሉ ተጠቃሚ አድርገዋል ያሉት ኃላፊው እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ 55 ሺህ ዜጎች ወደ ስራ የተሰማሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 44 ሺህ 223ቱ ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በያዝነው 2012 ዓ.ም አምስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች (ቦሌ ለሚ ቁጥር 1፣ ቂሊንጦ፣ ባህር ዳር፣ ጅማና ደብረ ብርሀን) ሲጠናቀቁ፤ ጊዜያዊ የስራ እድልን ሳይጨምር፣ በአጠቃላይ ለ20 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የሚናገሩት አቶ ደርቤ ሁለቱ (ቦሌ ለሚና ቂሊንጦ) ብቻ ለ10 ሺህ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ይናገራሉ።
አልፎ አልፎ የሃይል መቆራረጥ በዘርፉ ከሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች አንዱ መሆኑን የጠቆሙት ይህንንም ችግር ለመፍታት ባለሀብቶቹ እራሳቸው ከፀሀይ እና ከነፋስ (Solar system and Wind) ሀይል በማመንጨትና በመጠቀም ስራቸውን እንዲያከናውኑ እንዲደረግ ከመንግስት የተቀመጠ አቅጣጫ ስላለ በዚሁ መሰረት እየተሰራና እራሳቸውን እንዲችሉ እየተደረገ” መሆኑን ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች መቋቋም ዋና አላማ የውጪ ምንዛሪ ለማስገኘት፣ የስራ እድል ለመፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ነው የሚሉት አቶ ደርቤ ይህ ገና ከአሁኑ ውጤት እያመጣና የውጪ ምንዛሪንም ሆነ የስራ እድልን እየፈጠረ፤ ለወደፊቱም ተስፋ ሰጪ ዘርፍ እንደሆነ ነው የሚናገሩት።
መንግስት በተያዘው የበጀት አመት ለሶስት ሚሊዮን፤ በሚቀጥሉት 10 አመታት ውስጥ ደግሞ ለ20 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እየሰራ መሆኑና ይህንንም ለማስፈፀም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ “የስራ እድል ፈጠራና ኢንቨስትመንት መሪ ኮሚቴ”፣ እንዲሁም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ “የስራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት” ተቋማት መመስረታቸው የሚታወስ ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2012
ግርማ መንግሥቴ