አዲስ አበባ፡- በመዲናችን አዲስ አበባ የድምፅ ብክለት ከእለት ወደ እለት እየተባባሰ ከፍተኛ የጤና እክል እየፈጠረ መሆኑ ተገለፀ።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን የአካባቢ ህግ ትግባራ፣ ክትትልና ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ለሜሳ ጉደታ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት ምንም እንኳን አስፈላጊው ክትትልና ቁጥጥር ቢደረግና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ቢሰሩም በከተማዋ እየተስተዋለ ያለው የድምፅ ብክለት እየጨመረና ለነዋሪው ከፍተኛ የጤና ችግር እየሆነ ነው።
አቶ ለሜሳ እንደሚናገሩት በከተማዋ የድምፅ ብክለት ከሚያስከትሉ ተቋማት ውስጥ ከፋብሪካ የሚወጡ የተለያዩ ማሽኖችና ሞተሮች፣ መብራት ሲጠፋ የሚንቀሳቀሱ ጀነሬተሮች፣ በሞንታርቦ የሚነገሩ ማስታወቂያዎችና ንግዶች፣ በየሱቆች በር ላይ በትልልቅ ማይክራፎኖች የሚለቀቁ መዚቃዎች፣ ከሀይማኖት ተቋማት የሚሰሙ የድምፅ ማጉያዎች፣ የምሽት ዳንስና ጭፈራ ቤቶች፣ ከ”ሽሮ ቤት” የሚለቀቁ ሙዚቃዎች፣ ኮንዶሚኒየም አካባቢ ያሉ ግሮሰሪዎች፣ ወዘተ ተጠቃሽ ናቸው።
ይህን በከተማዋ እየተስተዋለ ያለውን የድምፅ ብክለት ለመቆጣጠርና ለማስቆም ህብረተሰቡ ያቀረበውን አቤቱታ መሰረት በማድረግ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን የገለፁት አቶ ለሜሳ ከማስጠንቀቂያና ገንዘብ ቅጣት ጀምሮ ድርጅቶቹን እስከ ማሸግ ድረስ መኬዱን ጠቅሰው በየካ አባዶ ብቻ በአንድ ጊዜ 15 ድርጅቶች መታሸጋቸውን፤ በ2011 ዓ.ም 300 የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል።
በተለይ በኮንዶሚኒየም አካባቢ ከግሮሰሪዎችና ቡና ቤቶች የሚወጣው የድምፅ ብክለት በከፍተኛ ደረጃ እየረበሸ፣ ጤና እየነሳና አካባቢውን ለተለያዩ ችግሮች እየዳረገ በመሆኑ ክትትሉ ጠንከር ያለ ነው የሚሉት ቡድን መሪው በእነዚህ አካባቢዎች ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥልም ይናገራሉ።
እንደ አቶ ለሜሳ አስተያየት ይህ የክትትልና፣ ቁጥጥር እርምጃ የመውሰድ እንቅስቃሴ በከተማዋ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ በተናበበና በተጠናከረ መልኩ እየተሰራ ይገኛል። በተለይ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እየተሰራባቸው ባሉ ወረዳዎች የተሻለ ውጤት እየታየ ሲሆን የህብረተሰቡ ትብብርና ጥቆማ በተቀዛቀዘባቸው ወረዳዎች ያለው ሁኔታ ግን ሊሻሻልና ነዋሪው ችግሩን ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ ይገባዋል።
የድምፅ ብክለትን እንቆጣጠር ስንል ዝም ብለን ለቅንጦት አይደለም የሚሉት ቡድን መሪው ብክለቱ ነዋሪውን በተለይም ህፃናትና አረጋውያንን ለነርቭ መታወክ፣ ለሆድ እቃ ህመም፣ ቀለምን መለየት ያለመቻልን ለመሳሰሉ አደገኛ በሽታዎች የሚዳርግ ከፍተኛ የጤና ጠንቅ በመሆኑና ህብረተሰቡ የእነዚህ በሽታዎች ተጠቂ እንዳይሆን በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የከተማው ነዋሪ በየአካባቢው የሚስተዋለውን የድምፅ ብክለት ለመቆጣጠርና ለመከላከል አስፈላጊውን መረጃ ከወረዳ ጀምሮ ላሉት የአካባቢ እንክብካቤ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች በመስጠት ትብብር ሊያደርግ እንደሚገባ ቡድን መሪው አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2012
ግርማ መንግሥቴ