ኢትዮጵያውያን በርካታ የሚያስተሳስሩንና የሚያጋምዱን ባህሎች አሉን። ብሄር፣ ቋንቋ፣ ሀይማኖት እና ጾታ ሳንለይ የምንተሳሰብባቸው፣ ፍቅራችንን የምንገላለጽባቸውና በችግር እና በደስታ ጊዜም የምንረዳዳባቸው ለዘመናት ያካበትናቸው በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶች አሉን። እነዚህ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እሴቶቻችን እንዳንለያይ አድርገው አጋምደውንና ብሄር፣ ቋንቋ፣ ሀይማኖት ብለን እንዳንለያይ አጣምረውን ለዘመናት በአብሮነት አኑረውናል። አሁንም በዚሁ መልኩ ተዋደን፣ ተከባብረን፣ ተቻችለን እየኖርን ነው። ይህንኑ ወደፊትም አጠናክረን ለልጆቻችንና ለልጅ ልጆቻችን የምናወርሰው መልካሙ ኢትዮጵያዊ ባህላችን ነው።
ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ በሚያጋጥሙ ፖለቲካዊ ችግሮች ይሄን አንድነታችንን ለመሸርሸር ጥረት ሲደረግ ይታያል። ተሳስቦ፣ ተከባብሮ እና ተቻችሎ የሚኖረውን ህዝብ በግል ወይም በቡድን ጥቅምና ፍላጎት ለመለያየትና ለማቃቃር፤ አንዱን ብሄር እና ሀይማኖት ከሌላው ጋር ለማጋጨት ሲሞከርም ይስተዋላል። ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች የታዘብነውም ይሄንኑ ነው። ፖለቲካዊ መነሻ ያለውን ግጭት ወደ ብሄር እና ሀይማኖት እንዲለወጥ በማድረግ ዜጎች ህይወታቸውን እንዲያጡ፤ የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው፤ ንብረትም እንዲወድም እና ከቤት ንብረታቸውም እንዲፈናቀሉ ሆነዋል። በማናቸውም መመዘኛ ይሄ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን መገለጫ አይደለም።
ሀገራችን የምትታወቀው በእንግዳ ተቀባይነት ነው። ኢትዮጵያውያን የምንታወቀው እንግዳ ሲመጣ ለራስ ሳይበላ እንግዳ ሲጋበዝ፣ መኝታ ለእንግዳ ሲለቀቅ፣ እግር አጥበንና ምግብና መጠጥ አቅርበን ስናስተናግድ ነው። በዓለም ላይ ኢትዮጵያ የምትታወቀው ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች የእምነት ልዩነታቸው እንደተጠበቀ ተዋደውና ተፋቅረው የሚኖሩባት አገር መሆኗ ነው። ሙስሊምና ክርስቲያን ባልና ሚስት፣ እህትና ወንድም፣ በአጠቃላይ አንድ ቤተሰብ ሆነው የሚኖሩባት ምድርም ናት አገራችን ኢትዮጵያ። በታሪክ የሚታወቀው፣ እየኖርን ያለንበትና እውነተኛው የኢትዮጵያውያን መገለጫችንም ይሄው ነው።
የተቸገረን ማብላትና መደገፍ፣ ያዘነን ማስተዛዘን፣ ደስታንና ሀዘንን በጋራ ማሳለፍ በሁሉም ብሄር የምናገኘው እሴታችን ነው። ሙስሊሙ በደስታው ቀንና በበዓሉ ወቅት ክርስቲያን ጎረቤት፣ ዘመድና ጓደኛውን አስቦ፤ ክርስቲያኑም በሰርግና በድግሱ በተመሳሳይ ተጨንቆና ተጠቦ ሁሉንም ወገኖቹን እኩል ባስደሰተ መልኩ ለማሳለፍ ጥረት ሲያደርግ ነው የምንታወቀው።
አሁንም በተለያየ መልኩ ችግሮች ሲያጋጥሙ አይዞህ ወገኔ የሚባባለው ብሄር፣ ዘር፣ ቋንቋና ሀይማኖት ሳይለይ በጋራ ነው። የከፋውን አስጠልሎና አደጋ እንዳይገጥመው ደብቆ ችግርን ያሳልፋል። የተጠማው ያጠጣል፣ የተራበውንም ያበላል። በአዳማ ተከስቶ በነበረው ግጭት ቤተክርስቲያን እንዳይቃጠልና ጉዳት እንዳይደርስበት ሲጠብቁ ያደሩት ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ሙስሊም ወገኖችም ጭምር ናቸው። መስጊድ እንዳይቃጠል የጠበቁትም ክርስቲያን ወገኖች ጭምር ናቸው። ይሄ በኢትዮጵያውያኑ ልብ ውስጥ በወርቅ ተጽፎ የሚቀመጥ ድንቅ ታሪክ ነው። ለነገም እንደ ሀገር በሰላም፣ በአንድነትና በብልጽግና ለመቀጠል የሚያስፈልገው ይሄው አንድነትና ህብረታችን ነው።
በሀገራችን በተለያየ ቦታ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ሲፈናቀሉ ሌላው ወገን የዕለት ዕርዳታ በማሰባሰብ ሲያግዛቸው እንደነበር እናስታውሳለን። በጅግጅጋ በነበረው ሁከትና ረብሻ ጥቂቶች ጥቃት ቢያደርሱም ብዙሀኑ የክልሉ ነዋሪ በወገኖቻችን ላይ ጥቃት እንዳይደርስ በቤታቸው ሸሽገው ሲያኖሩና ነፍሳቸውን ሲያተርፉ አይተናል። በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልልና በሌሎችም አካባቢዎች መፈናቀል ሲያጋጥም ያለውን በማካፈል ወገናዊነቱን ያረጋገጠው ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያለው ሁሉም ህዝብ ነው።
በቡራዩ አካባቢ በነበረ የችግር ወቅትም የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ነዋሪውን በማስተባበር ለተጎጂው የተለያየ ሰብአዊ ድጋፍ በማድረግ ወገናዊነታቸውን አስመስክረዋል። ሰሞኑን በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ባጋጠመው ችግር ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉና ለተጎጂዎች በአዲስ አበባ “የሰብአዊ ድጋፍ ጥምረት” በሚል በሀገር ፍቅር በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ እናቶች በጀርባቸው ሳይቀር ሰብአዊ እርዳታ ይዘው በመምጣት ለወገኖቻችን እርዳታና ድጋፍ በማድረግ ኢትዮጵያዊ ወገንተኝነታቸውን አስመስክረዋል።
የኢትዮጵያውያን የመረዳዳት እና የመተሳሰብ ባህል በችግር ወቅት ብቻም አይደለም። በደስታ ጊዜም ትብብሩን ለማየት ተችላል። በቅርቡ እንኳን የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ በተከበረበት ወቅት የከተማው ነዋሪ ገንዘብ አዋጥቶ የሚበላና የሚጠጣ ውሀ በየመንገዱ ዳር በማዘጋጀት የኦሮሞ ህዝብን አስተናግዶ በክብር ተቀብሎ በክብር ሸኝቷል። የኢትዮጵያውያን ባህል ይሄ ነው። መከፋፈል፣ ጭካኔ የተሞላው እንቅስቃሴ ማድረግ ባህላችን አይደለም!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2012