ጥቂት እጆች ለጥፋት በተዘረጉበት ቅፅበት ወገን ከየአቅጣጫው ተሰብስቦ እኩይ ተግባርን በመልካም ሥራ የመከተበት የመጀመሪያ ቀን፤ አገር ስትታመም መልካሞች እኩይ እጆችን በበጎነት ያሸማቀቁበት የትብብር መንፈስ፤ በአገር ፍቅር ቲያትር ቅጥር ግቢ ደርሶ የሚሆነውን ላስተዋለ በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶና ልቡ ሞልቶ ይመለሳል። ጥቂቶች ሲያፈናቅሉ እልፎች የወደቁ እናቶችን፣የተገፉ አባቶችን፣የሰብአዊነት ጥጋት የሚፈልጉ ህፃናትንና ልባቸው የተሰበረ ወጣቶችን ሊያበረቱ ሸክማቸው ሲካፈሉ፤ጭንቀታቸውን ሲጨነቁ ይታያል።
በግቢው ውስጥ እጃቸውን ለሰብአዊነት ለመዘርጋት ከመጡት ውስጥ ወጣት ያሬድ ግርማን ጠጋ ብዬ አናገርኩት። ከወንድሙ ጋር ነበር። ሰሞኑን በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ፅንፈኞች በዜጎች ላይ በሰነዘሩት ጥቃት የደረሰባቸውን የከፋ ጉዳት እና ችግር ለመካፈል የአቅማቸውን ለመርዳት መምጣታቸውን አጫወተኝ። ፊቱን ቅጭም አድርጎ በሆነው ነገር ማዘኑን ይናገራል። ወገን በወገኑ ላይ ይህን መሰል አፀያፊ ድርጊት መፈፀሙና ግጭት መከሰቱን ያወግዛል ‹‹በግጭቱ ብዙ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል›› የሚለው ያሬድ በዚህ አስከፊ ጊዜ የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ስለተረዱ ካላቸው በመቀነስ የንፅህና መጠበቂያ ቁሶችን እና ለምግብነት የሚውሉ ጥራጥሬዎችን ለእርዳታ አሰባሳቢው ኮሚቴ ማስረከባቸውን ተናግሯል።
ዳንኤል ገብረመድህን ሰብአዊ ድጋፉን በበጎ ፈቃድ የሚያሰባስበው ‹‹የሰብአዊ ድጋፍ ጥምረት›› አባል ነው።‹‹ከቤታቸው ተፈናቅለው መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች በየእለቱ የሚያስፈልጋቸው ብዙ ድጋፍ አለ›› በማለትም የአልባሳትና ምግብ ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ይናገራል። ከአዲስ አበባ እና ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች አስደናቂ ምላሽ እንዳገኙም ይገልፃል። ከግለሰቦች ብቻ ከትንሽ እስከ መቶ ሺህ ብር የሚገመቱ ደረቅ ምግቦችንና አልባሳትን በየቀኑ እያሰባሰቡ መሆናቸውን ይገልፃል። ሁሉም በዚህ ድጋፍ ላይ እንዲተባበር ያደረገው ‹‹ሰው መሆን ብቻ›› እንደሆነ በማንሳትም ከውጪም ሆነ ከመላው አገሪቱ እየመጣ ያለው ድጋፍ ኢትዮጵያዊነት ከሰብአዊነትና ከመደጋገፍ የማይነጣጠል መሆኑን ያነሳል።
‹‹በሁለት ቀን ጥሪ ብቻ በርካታ ህዝብ እጁን ለወገኖቹ መዘርጋቱና ድጋፍ ማሳየቱ ትልቅ ትርጉም አለው›› በማለት አስተያየቱን የሚሰጠው የዝግጅቱ ዋና አስተባባሪ ያሬድ ሹመቴ ነው። በተደረገው የሰብአዊ ድጋፍ ማሰበሰብ ፕሮግራም እስከ 12 ሚሊየን ብር የሚገመት ቁሳቁስ ተገኝቷል። ኢትዮጵያዊያን በዚህ መንገድ መተባበራቸው የሚገርም ባይሆንም ይህ ባህል ጠፍቷል ተብሎ እንዳይታሰብ ትልቅ ማሳያ ነው። የማህበረሰቡ አዕምሮ ውስጥ የጠፋው ትልቁ ትዝታ መተሳሰብ፣አንድነት፣ህብረት በዚህ አይነት መንገድ መገለፅ መቻሉ ተስፋ እያጣ ለመጣው ህዝብ ተስፋ መልሶ የሚሰጥ ስለሆነ መተሳሰቡ መቀጠል እንዳለበት ይናገራል።
‹‹ሁሌም ሰብአዊነት መቅደም ይኖርበታል›› ያለው ወጣት ያሬድ ኢትዮጵያውያን የፈጠሩትን ችግር የሚፈቱት ኢትዮጵያውያን ናቸው። ለዚህ ደግሞ መተባበር ያስፈልጋል ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል። የተፈጠረውን አለመረጋጋት እና እየተወሰደ ያለውን የመፍትሄ እርምጃና የሰብአዊ ድጋፍ አስመልክተው የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪተሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን የአዲስ አበባና ከተለያዩ ክልሎች ወጣቶች ከመንግሥት ጋር በመነጋገር አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የምግብና የአልባሳት እርዳታ ለተጎዱ ወገኖች ማድረሳቸውን አንስተዋል። አገር ከማረጋጋት ጎን ለጎን ይህ አይነቱን ሰብአዊ ተግባር እየፈፀሙ ላሉ ወጣቶችም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2012
ዳግም ከበደ