አዲስ አበባ፡- የክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ድርጅት ማህበራት ህብረት /ሲአርድኤ/ ህዳር 10/2012 ዓ/ም ሊደረግ ለታሰበው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ አንድ ሺህ ታዛቢዎችን እያዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ።
የህብረቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ንጉሱ ለገሰ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ ለአገራዊ ምርጫው የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ ጎን ለጎን ደግሞ ለሲዳማ ህዝበ ውሳኔ አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶችን እያደረገ ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ ከፋይናንስ ጀምሮ ችግሮች አጋጥመዋል ያሉት ዶክተር ንጉሱ፣ ሆኖም ግን ህዝበ ውሳኔው ልምድን የሚያጋራና ለቀጣይ ምርጫ ድጋፍ የሚያደርግ በመሆኑ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል። እስካሁንም 800 ለሚደርሱ አባላት ስልጠና ተሰጥቷል። እስካሁን እንደታወቀው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የሚካሄደው በ1ሺ600 የምርጫ ጣቢያዎች መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም በታዛቢነት ተሳታፊ የሚሆኑ አንድ ሺህ ሰዎች ለማቅረብ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ህብረቱ በአሁኑ ወቅት እየሰራ ያለው በህዝቡ ዘንድ የተረጋጋ ሰላም መፍጠር ላይ እንደሆነ የሚያስረዱት ዶክተር ንጉሱ፣ ሰላሙን ሊያደፈርሱ የሚችሉ አካላትን አጋልጦ በመስጠትና እንዲታረሙ ለማድረግ ከህዝቡ ጋር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል። ከህዝቡ ጋር በቅርበት ሆኖ ማገዝና ሰላማዊ ህዝበ ውሳኔ እንዲከናወን ማድረግ የህብረቱ አንዱ ድርሻ ነው ያሉት ዶክተር ንጉሱ ፣ከዚህም ባለፈ መንግሥትን በገንዘብና በተለያዩ መንገዶች የመደገፍ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በሲዳማ የህዝበ ውሳኔ ድምጽ በሚሰጥባቸው ጣቢያዎች ክትትል ማድረግና የመታዘብ ሥራ ይሰራል ብለዋል። ለዚህም ሥራ የተመረጡት ዲግሪና ከዚያ በላይ ትምህርት ያላቸው እንዲሁም በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የተቀመጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው