• ከ116 ወረዳዎች በሳምንት ሰባት ቀናት ውሀ የሚያገኙት 12ቱ ብቻ ናቸው
አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ የውሃ አቅርቦትን ችግር በመሰረታዊነት ሊፈቱ የሚችሉ ፕሮጀክቶች ግንባታ መጓተት ውሀን በፈረቃ መስጠቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረጉን የአዲስ አበባ ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን አስታወቀ።በከተማዋ በውሀ ፈረቃ ውስጥ ያልገቡት 12 ወረዳዎች ብቻ ናቸው።
የባልስጣኑ የኮሙዩኒኬሽን የስራ ሂደት ቡድን መሪ ወይዘሮ ሰርካለም ጌታቸው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት በተለይ ከውጭ ምንዛሬ እና የወሰን ማስከበር ችግር ጋር በተያያዘ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ምርት አለመግባታቸው በምርት እና ፍላጎት መካከል ከፍተኛ ልዩነት ተፈጥሯል።
ባለስልጣኑ አሁን ያለው አቅም በቀን 580 ሺ ሜትር ኪዩብ ሲሆን ፍላጎቱ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ መሆኑን ጠቁመው ይህንን የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ችግር ለመቅረፍ ውሃ በፈረቃ እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል። በአዲስ አበባ በሚገኙ 116 ወረዳዎች በፍትሃዊ መንገድ ውሃ እንዲደርሳቸው ስራ እየተሰራ ነው ያሉት ወይዘሮ ሰርካለም በሳምንት ሰባት ቀን ውሀ የሚያገኙ ወረዳዎችን በመለየት ከሚያገኙትን የውሀ መጠን በመቀነስ ለሌሎች ወረዳዎች እንዲደርስ የማድረግ ስራ ተሰርቷል።ባላቸው የቦታ አቀማመጥ የተነሳ ይህን ማድረግ የማይቻልባቸው አካባቢዎች ደግሞ በቦቴ ውሃ የማቅረብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሳምንት አንዴ ውሃ የሚያገኙት 20 ወረዳዎች፣ በሳምንት ሁለት ወይም ሦስት ቀን የሚያገኙ 29 ወረዳዎች ሲሆኑ ከአራት እስከ አምስት ቀን የሚያገኙ ደግሞ 25 ወረዳዎች መሆናቸውን ገልጸው በሳምንት ሰባት ቀን የሚያገኙት 12 ወረዳዎች ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ችግሩን የሚፈታው በ2011 ዓ.ም የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ጨርሶ ወደ ሥራ ማስገባት ሲችል መሆኑን አስታውቀዋል።በ2011 ዓ.ም ተጀምረው ዘንድሮ የማጠናቀቅ ስራ ከሚሰራባቸው የውሃ ፕሮጀክቶች መካከል አለም ባንክ አካባቢ ፣የሺደበሌ ፣ጀሞ ሚካኤል ፣አረቄ ፋብሪካ፣ሳሪስ አዲስ ሰፈር ፣ካራ ፣ቄራ፣ ሆላንድ ኤምባሲ፣ሸጎሌና ቤተ መንግሥት አካባቢ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከሸጎሌና ከሆላንድ ኤምባሲ ውጪ ሌሎች ቦታዎች የፕሮጀክቶቹ ቁፋሮ የተጠናቀቀ ሲሆን በቅርቡም አገልግሎት እንደሚሰጡ ጠቁመዋል። እነዚህ 12 ጉድጓዶች ተጠናቀው ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መሰጠት ሲጀምሩ በቀን 6ሺ 480 ሜትር ኪዩብ ውሃ የሚመረት እና 60 ሺ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2012
አብርሃም ተወልደ