ቢሾፍቱ፡- በባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ በቢሾፍቱ ከተማ የነበረው የሰላም መደፍረስ ትምህርት ሰጥቶ ያለፈና የከተማዋን ህዝብም ሰላም ፈላጊነት ያሳየ እንደነበር ተገለጸ።
የቢሾፍቱ አስተዳደር ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ሽፈራው እንደገለጹት፤ በከተማዋ ተከስቶ የነበረው ግጭት እንደ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ ነው። ሁነቱም የከተማዋ ህዝብ ከምንም በላይ ሰላም ፈላጊ መሆኑን በተግባር ያሳየበት ክስተት ነበር። እንደ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ገለጻ፤ ከተማዋ አሁን ተረጋግታለች፤ ወደነበረ ሰላሟም ተመልሳለች። ይህ ደግሞ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቱ፣ የከተማው ነዋሪና የፀጥታ ሃይሉ ሰላሙን ለማረጋገጥ በእኔነት ስሜት ተቀናጅተው የመስራታቸው ውጤት ነው።
ተቋርጠው የነበሩ የመንግሥት ስራዎችም ሆኑ ሌሎች የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች፤ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ እንዲሁም ህዝባዊ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወደሥራ ገብተዋል ያሉት ወይዘሮ ዓለምጸሃይ ይሁን እንጂ ክስተቱ ብዙ ያስተማረ፣ የከተማዋ ህዝብም ከምንም በላይ ሰላም ፈላጊ መሆኑን ያሳየበት ነው ብለዋል።
የከተማዋ ሰላም እንዲመለስ ህዝቡ ከጸጥታ ሃይሉና ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በመሆን መስራቱን ጠቅሰው በሚያደርጋቸው የሰላም ኮንፍረንሶችም የብሔርና የሃይማኖት ገጽታን ሽፋን በማድረግ የሚከናወኑ ሰላምን የማደፍረስ እንቅስቃሴዎችን ለመመከት እየሰራ ይገኛል።
በከተማዋ የ02 ቀበሌ ነዋሪ የሆነው ወጣት ሞኢቦኒ ካሳ እንደሚለው፤ ሁነቱ የሚያሳዝንም የሚያስቆጭም ነበር። ተግባሩም የህዝብን ሰላምና አብሮነት የማይፈልጉ ሃይሎች እንጂ የከተማዋ ህዝብና ወጣት ፍላጎት አይደለም።በመሆኑም ችግሩ ወደባሰ አደጋ ሳያመራ በህዝቡ፣ በወጣቱና በጸጥታ ሃይሉ ቅንጅት ተገትቷል።
አሁንም እነዚህ ሃይሎች የሚተኙ ባለመሆናቸው ህብረተሰቡንም ሆነ ወጣቱ ሊጠቀሙበት ከሚፈልጉ ሃይሎች ራሱን ሊጠብቅ ይገባል ያለው ወጣት ሞኢቦኒ የተፈጠረው ሰላም ዘላቂ እንዲሆንም ህብረሰተቡ ከጸጥታ ሃይሉ ጋር ሊቀናጅ፤ መንግሥትም የህዝቡን ጥያቄ ተገንዝቦ ሊሠራና የሕግ የበላይነትን ሊያረጋግጥ ይገባል ብሏል።
በከተማዋ የ07ቢፍቱ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ፀጋዬ ደርቤ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ቢሾፍቱ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና እምነቶች በአንድነት የሚኖሩባት ሰላማዊ ከተማ ናት። የሰሞኑ ክስተትም ሊሆን የማይገባው ነው። ሆኖም ህዝቡ፣ ወጣቱና የጸጥታ ሃይሎች በጋራ በመስራታቸው ችግሩ ሊበርድና ከተማዋም ልትረጋጋ ችላለች።
አሁን የተገኘው አንጻራዊ ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው በትኩረት ሊሰራ ይገባል። ለዚህም ወጣቱ፣ ህዝቡ፣ የጸጥታ ሃይሉ እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ለጋራ ሰላሙ ተባብረው ሊሰሩ፤ ጥያቄዎች ካሉም በሰላማዊ መልኩ ሊያቀርቡ ይገባል። የከተማ አስተዳደሩ በሂደቱ ተሳታፊ ናቸው ያላቸውን 38 ተጠርጣሪዎች ይዞ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ከአስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2012
ወንድወሰን ሽመልስ