አዴፓ፣ አብን እና አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጥምረት የያዘው የአማራ ድርጅት የስምምነቱ አካል ሆነዋል። የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች እና ጥቅሞች ምላሽ እንዲያገኙም ፓርቲዎቹ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በአማራ ምሁራን መማክርት ጉባዔ አዘጋጅነት በአማራ ክልል እና በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በውይይት መድረኩ በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው የአማራን ሕዝብ አማክለው የሚቀሳቀሱት አዴፓ፣ አብን እና አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት የአማራ ድርጅት ከፍተኛ መሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተሳትፈውበታል።
ፓርቲዎቹ ከውይይታቸው በኋላ የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች እና ጥቅሞች ምላሽ እንዲያገኙም በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በአማራ ክልል ብሎም በሀገሪቱ ሠላም፣ አንድነት እና ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና የሕግ የበላይነት እንዲከበርም በተባበረ ክንድ ለመሥራት ተስማምተዋል።
የአማራ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥቅሞች እንዲረጋገጡ፣ ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች የሚደርስባቸውን ግፍ እና በደል ለማስቆም እና መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር ፓርቲዎቹ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ሰሞኑን በአንዳንድ የኦሮሚያ እና ሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ አካባቢዎች በንጹሐን ዜጎች ላይ በደረሰው የሞት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ፓርቲዎቹ ገልጸው ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትን ተመኝተዋል። የወንጀሉ ተሳታፊዎችም በሕግ እንዲጠየቁና ለተጎጂዎችም ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቅርበዋል ሲል የአማራ ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ ዘግቧል።
አዲ ዘመን ጥቅምት 23/2012