አዲስ አበባ ፡- ኢትዮጵያ ከትምባሆ ነጻ የሆነ አካባቢን ለመፍጠር የደነገገችውን አዋጅ በጣሱና አካባቢያቸውን ለሲጋራ፣ሀሺሽና ሺሻ መጠቀሚያ አድርገዋል በተባሉ ሆቴሎችና ተቋማት ላይ ርምጃ መውሰድ መጀመሩን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባ ለስልጣን የ ምርት ደ ህንነት ዳይሬክተር ወይዘሮ አስናቀች ዓለሙ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ በነዚህ ሆቴሎችና መሰል ተቋማት ላይ እርምጃውን መውሰድ ያስፈለገው በሀገሪቱ በአዋጅ የተደነገገውን የሲጋራ ማጤስ ህግ በመጣስ በተከለከሉ ሥፍራዎች ላይ ሲጋራና ሀሺሽ ማስጨሳቸው በማስረጃ በመረጋገጡ ነው፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ትምባሆ በሰው ልጆች ማህበራዊና ኢኮኖሚ እንዲሁም በአካባቢዎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል የሚያስችለውን አዋጅ ቁጥር 1112/2011 አጽድቋል፡፡አዋጁ ከዓለም የጤና ድርጅት የትምባሆ ስምምነት ጋር የሚጣጣምና ጠንካራ ማዕቀፍ የተሰጠው ጭምር ነው፡፡
ስምምነቱን ኢትዮጵያ እኤአ በ2014 ህጉን ተቀብላ ያጸደቀች ሲሆን፣ አፈጻጸሙን ተግባራዊ ለማድረግም የትምባሆ ማጤስ ክልከላውን ከሚደግፉ ተቋማት ጋር በመሆን በተለየ ትኩረት ስትንቀሳቀስ ቆይታለች፡፡
ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ሲጋራና መሰል ሱስ አስያዥ ነገሮች እንዳይጨሱ የሚከለክለው አዋጅ በመላው ሀገሪቱ ጸድቆ ተግባራዊ ከመሆኑ አስቀድሞ በተለያዩ ስፍራዎች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ሲከናወን ቆይቷል ያሉት ወይዘሮ አስናቀች ይህ ከሆነ በኋላ ግን በአንዳንድ ሆቴሎችና ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ተቋማት አካባቢ ህጉን የሚተላለፉ ተግባራት ስለመከናወናቸው መረጃዎች ተገኝተዋል ብለዋል፡፡
ባለፉት ሶስት ወራት በአዲስ አበባ ከተማ ከትንባሆ ነጻ መሆን የሚገባቸው 3ሺ200 የተመረጡ ተቋማትን ለመቆጣጠር በተደረገው እንቅስቃሴ 587 ለሚሆኑት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ 40 የሚሆኑ የሆቴልና ሬስቶራንት ባለቤቶችንም በወንጀል በመጠየቅ እስከመታሰር የሚደርስ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ከአንድ በላይ ኮከብ ባላቸው 175 ሆቴሎች ላይ በተደረገው ቁጥጥር በሰባ ስድስቱ ላይ የተለያዩ ርምጃዎች በመውሰድ ክልከላ በተደረገባቸው ሌሎች የጤና ተቋማትና የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሂደቱ ስለመቀጠሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ እኤአ በ2016 በተደረገው ጥናት በኢትዮጵያ 3ነጥብ አራት ሚሊዮን ህዝብ የትምባሆ ጢስ ሰለባ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ በተደረገው ጥናትም 12 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነው የስራ ቦታ ለትምባሆ ጢስ የተጋለጠነው፡፡ከዚሁ ጥናት ጋር ተያይዞ በደባል አጫሾች ላይ ያለውን ተጽእኖ ጭምር ለመቀነስ የሚያስችል የግንዛቤ መፍጠር ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡በግንዛቤውም በርካታ ተቋማት ህጉን ተቀብለው ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የህግ ባለሙያው አቶ ዳግም አለማየሁ በበኩላቸው ዕድሜያቸው ከሃያ አንድ ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎችና ወጣቶች ትምባሆን የሸጠ ማንኛውም ሰው ከሶስት ወራት ያላነሰ እስርና ከሶስት ሺህ እስከ አምስት ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣልበት ይናገራሉ፡፡
ማንኛውም ሰው ለህዝብ ክፍት በሆነ ማንኛውም ቦታ በህዝብ መጓጓዣዎችና በጋራ መኖሪያ ቤቶችና በትምህርት ቤቶችና መሰል ስፍራዎች ላይ ሲጋራን በማጤስ የሌሎች ጤንነት ማወክ እንደማይገባው በመጠቆም በተመሳሳይ ሁኔታም የትምባሆ ማጤስ ክልከላው ባለባቸው ስፍራዎች በ100 ሜትር ዙሪያ ሲጋራን መሸጥ እንደማይገባም ሕጉን አጣቅሰው ያስቀምጣሉ፡፡እነዚህንና ሌሎችንም ህጎች ተግባራዊ ለማድረግ ወንጀል ፈጻሚዎቹን ከመጠቆም ጀምሮ ለህግ አካላት አሳልፎ እስከመስጠት መላው ህብረተሰብ ሊተባበር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በህግ ድንጋጌ ያጸደቀቸው የትምባሆ ጢስን የመቆጣጠር አዋጅ በዓለም ጤና ድርጅት ምስጋናና አውቅና የተቸረው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ፓርላማ አባላትም ለዚሁ እንቅስቃሴ አድናቆትና ሽልማት የተቸራቸው ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2012
መልካምስራ አፈወርቅ