ግጭቶች የአብሮ መኖር አንድ ክስተቶች ናቸው። እናም በመላ ሲያዙ የራሱ የችግሩ መፍቻ መንገዶች ሆነው ቀጣዩን ማህበራዊ ህይወት ያለመልማሉ። በአንጻሩ አባባሽ ጉዳዮች ከታከሉባቸው ይበልጥ ይሰፉና ከባድ ጥፋት ያደርሳሉ። በአሁኑ ወቅት በእኛ አገር እየታየ ያለው ይኸው ነው። ታዲያ ከግጭቶች ለመማርና ለወደፊቱ ተጠቃሚ ለመሆን መለኛ መሆንና ችግሮቹን በአግባቡ መፍታት ያስፈልጋል።
የግጭት አያያዝና አፈታተ ሲነሳ ባለሙያዎች ሁልጊዜ የሚያወሱት አንድ በደቡብ አፍሪካ በጫካ ውስጥ የሚኖሩ ማህበረሰቦች ልምድ አለ። እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች በአደን የሚኖሩ በመሆናቸው የሚይዟቸው ጦርና ቀስቶች ናቸው። ጦርና ቀስቶቹ ደግሞ በመርዝ የተነከሩ ናቸው።
በዚህም ታዳኙን እንስሳ በመውጋት ብቻ ሳይሆን በመመረዝም የሚገድሉበት መንገድ ነው። ታዲያ እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች በመካከላቸው አለመግባባት ሲፈጠርና ግጭት ሲነሳ የሚፈቱበት መንገድ ብልህነት የተሞላበት ነው።
እናም ግጭቱ ሲከሰት ሁሉም አባላት በሽማግሌዎች አማካይነት ይሰባሰቡና በእጃቸው የሚገኙትን ጦር መሳሪያዎች በማውረድ በአንድ ሰው አማካይነት በጫካው ውስጥ ከርሱ በስተቀር በማይታወቅ ቦታ ይደበቃሉ። ከዚህ በኋላም በአንድ ላይ ተቀምጠው ውይይት ይጀምራሉ። በውይይታቸው መሀል የሚያስቆጣ ሁኔታ ቢፈጠር እንኳን የተበሳጨው ሰው ከመሀል ተነስቶ ስሜቱ እስኪበርድለት ገለል ይላል እንጂ ፈጽሞ ለርምጃ አይጋበዝም።
በዚህ መልኩም አልቦ ጦርና ቀስት ችግራቸውን በውይይት ይፈታሉ። ይህ እስኪሆን ግን ቀናት ያልፋሉ እንጂ፤ አንዳቸውም ወደመሳሪያቸው አይቀርቡም፤ ጉልበትንም እንደችግር መፍቻ አይጠቀሙም። ይህ ሁሉ የሚሆነው ደግሞ በሽማግሌዎቻቸው አማካይነትና ለሽማግሌዎች ባላቸው ተገዥነት ነው። አዎን ሽማግሌ የማይረታው ውይይት የማይፈታው አንዳች ችግርም ሆነ ግጭት የለም። እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን?
እኛ ኢትዮጵያውያን ለእድሜ ባለጸጎች፤ ለአሸማጋዮችና ለእምነት አባቶች ትልቅ ከበሬታ አለን። ይህ በሁሉም ባህሎቻችንና እምነቶቻችን ጸንቶ የቆየ የማንነታችን መገለጫና የጋራ ሀብታችን የሆነ እሴት ነው። በየትኛውም ባህል ውይይት የማይፈታውና ሽምግልና የማይዳኘው ጉዳይ የለም።
ይህ ደግሞ ልጅ አዋቂው፤ ወጣት ሽማግሌው ተው ሲባል ስለሚሰማና ወደጥሞናው ስለሚመለስ ነው። ትልቁ ነገር ግን ወደ አሸማጋዩ መቅረብ ወይም ወደ ውይይት መድረኩ መምጣቱ ነው።
በአሁኑ ወቅት በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ያለመረጋጋቶቸ ይስተዋላሉ። እነርሱን ተከትሎም ግጭቶች ነበሩ። በዚህም ሆን ተብሎ በሚሰራጩ የሚያጋጩ ወሬዎችና ማን እንዳለና ምን እንደተባለ በማይታወቅበት ሁኔታም ጭምር ሰዎች በቡድን ተነስተው፤ ሁከት ተፈጥሮ ህይወት ጠፍቷል፤ አካል ጎድሏል፤ ንብረትም ወድሟል።
ወንድም በወንድሙ ላይ እንዴት እንዲህ ያለ ጥቃት ይፈጽማል? ተበደልኩ ባይ እንኳን ቢኖር ከውይይት ባለፈ እንዴት መብትን በጉልበት ለማስከበር ይነሳል? ይህስ አግባብ ነው ወይ? ሰው ጥያቄው እንዲሰማለት፤ የሚደግፈው እንዲነገርለት ህይወት ማጥፋት ያስፈልገዋልን?
በርግጥ ያለንበት የለውጥ ጉዞ መንገዱ ሁሉ ሳንካ አልባ አይደለም። ሙሉ በሙሉ ይሆናል ብሎ መጠበቅም አይቻልም። መሆን ያለበት ግን የሚያጋጥሙ ችግሮችን በአስተዋይነትና በሆደ ሰፊነት ጉዳት ሳያስከትሉ፤ ቂምንም ሳይወልዱ መፍታት ብቻ ነው። መንግስትም ህዝብም ከዚህ እምነት ውጪ አይደሉምና ይፈተናሉ።
ዋናው ጉዳይም መፈተኑ ሳይሆን ፈተናውን ማለፉ ነው። ግጭቶች የባሰ ሳይጠነክሩ ውጤታቸውም ከዚያ በላይ ሳይከፋ በብልሃት ማረቅ ያስፈልጋል። በአሁኑ ሰዓት ማረቂያ መንገዱ ደግሞ ውይይት እና መነጋገር ብቻ ነው።
በመሆኑም፤ የተነሱብንን “እኔንና የእኔን ብቻ” አጉል ወጎች ወዲያ ገፍተን፤ ቀድሞ የነበረንን የመከባበርና የመደማመጥ ልምዳችንን ተጎናፅፈን በጋራ ተቀምጠን “ችግሮች” የምንላቸውን ሁሉ ጉዳዮች በንግግር መፍታት አለብን። አዎን ዛሬ ታላቅ ታናሹን ሊገስፅ፤ አዋቂ አላዋቂውን በዕውቀት ሊያንፅ ይገባዋል።
እንዲህ አይነቱ ማህበራዊ መስተጋብራችን ከመቼውም በላይ ዛሬ ያስፈልገናል። አገራችን የእምነት አገር ናት፤ እኛም አማኞች ነን ካልን ከመቼውም በላይ ሁሉም እምነቶቻችን የሚጋሩትን ፈጣሪን መፍራት እና ወንድምን መውደድ የሚሉ መርሆዎችን ማክበር ይኖርብናል።
በዚህ ረገድ፤ ሰሞኑን በየአካባቢው የተጀመሩ ህዝባዊ ውይይቶች ሃሳብን የመግለጫ፤ ኩርፊያን ማብረጃ፤ የተራራቁትን ማቀራረቢያ መድረኮች ናቸውና ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። በተለይ በሰሞኑ የነበሩ ግጭቶች እና ትኩሳቶች በታዩባቸው በአዳማ በቢሾፍቱ በባሌ ሮቤ የተደረጉ ውይይቶች በአካባቢው የነበሩትን ችግሮች ከመፍታት ያለፈ ፋይዳ ሊኖራቸው ይገባል። መድረኮቹ እስከአሁን በአንፃራዊነት በሰላም ያሉ አካባቢዎች ፀጥታ እንዳይደፈርስ ተሞክሮ የሚቀሰምባቸው ልክ እንደጅማው ሁሉ ህዝብ የሚማማርባቸው ሊሆኑ ይገባል።
መንግስትም እነዚህን ህዝባዊ ውይይቶች ያላቸውን ፋይዳ ተረድቶ የየአካባቢውን ህብረተሰብ በመቅረብ ችግሩን ሊያዳምጥ፤ ፍላጎቱን ሊረዳ፤ ከዚያም አቅሙ በፈቀደው መጠን መፍትሄ ለመስጠት መስራት ይጠበቅበታል።
ወጣቶችም ነገሮችን እና ሁኔታዎችን በግብታዊነት ተቀብሎ ስሜታዊ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበው እያንዳንዱን ክስተት በብስለት መመርመርና የርምጃቸውንም ክፉና መልካም ውጤት መዝነው ህዝባቸውንና አገራቸውን በሚጠቅሙ ድርጊቶች ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል።
በመሆኑም፤ በአሁኑ ወቅት የተጀመሩ ህዝባዊ መድረኮችና ውይይቶች በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። ሽማግሌ ባለበትና ችግርን በሰከነ መንፈስ ተወያይቶ መፍታት በሚቻልበት ዘመንና አገር ጉልበትን እንደ አማራጭ መጠቀም ተገቢ አይደለም።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/2012