አዲስ አበባ:- መንግሥት ወጣቶች ዋጋ የከፈሉበትን የለውጥ አጀንዳ እየደረሰበት ካለው የተለያዩ የሴራ ጥቃቶች ለመታደግ ርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ። በመጪው አሥር ዓመታት ለ20 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ስትራቴጅክ እቅድም ይፋ ሆነ።
የመጀመሪያው አገር አቀፍ የሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ጉባኤ በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ሆቴል “አመርቂና ዘላቂ የሥራ እድል ለሁሉም” በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ ተገኝተው ጉባኤውን በይፋ ያስጀመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ ወጣቶች ዋጋ የከፈሉበትን የለውጥ አጀንዳ እየደረሰበት ካለው የተለያዩ የሴራ ጥቃቶች ለመታደግ አጥፊዎች ከእኩይ ተግባራቸው እንዲመለሱ ከማስተማር ጎን ለጎን መንግሥት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ የህግ የበላይነትን ማስከበር ዋነኛ ትኩረቱ እንደሚሆን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች በሚፈጠሩ ግጭቶች በርካታ የሰው ህይወት እየጠፋና ንብረት እየወደመ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ደመቀ፤ “ውስን አካላት ለውጡ የፈጠረውን እድል በአቋራጭ በመጥለፍ የሥራ እድል ፈጥሮ ጠንካራ የልማት አቅም ከማድረግ ይልቅ፣ ፍጹም አፍራሽ በሆነ ተልዕኮ ሲሰማሩ ይስተዋላል።
በዚህ እኩይ ሀሳብ መነሻም ከችግር መሻገርና ትውልዱን ማሻገር ተስኖን ባልተገቡ ግጭቶች ውስጥ ተጠምደን የድሃ ህይወት እንደዋዛ እየተቀጠፈ፣ የተሰራው እየወደመ፣ ያፈራነው እየጠፋ፣ ለዘመናት የገነባነው የአብሮነት ውሃ ልክም እየፈረሰ ይገኛል” ብለዋል።
በዚህ ዘመን ከመጠፋፋትና ከመጠላለፍ ጨዋታ በመውጣት፤ ታላቅ ራዕይ በመሰነቅ ሁሉም ዜጋ የሚኮራባትን ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መረባረብ እንደሚገባ ያሳሰቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሌሎች አገሮች የሌላቸውን እየፈጠሩ ታላቅ ሁነዋል። ለታላቅነትም ሲሯሯጡ ይስተዋላል።
ነገርግን፣ ኢትዮጵያውያን ብዙ ለታላቅነት የሚያበቃ ጸጋ እያለን፣ ወደ ትንሽነት ለመውረድ እየተጠላለፍን እንገኛለን። በዚህ በሰለጠነ ዘመን መሆን የሚገባው በለውጡ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታና የሰነቅነውን ተስፋ በማንገብ ወጣቱ ትውልድ በተለያዩ የማንነት ጠርዞች ሳይቆም እራሱን ከግጭት አምባ አርቆ በፍሬያማ የሥራ እድል ፈጠራ ላይ በማተኮር የህዝቡና የአገሪቱ ዋነኛ ጠላት በሆነው በድህነትና ኋላቀርነት ላይ መዝመት እንደሚገባ አሳስበዋል።
አሁን ላይ በተለያዩ ጠርዞች በመቆም በመጠፋፋት እጅግ አሳዛኝ ክስተት እየተስተዋለ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ትውልዱ በስክነትና በብስለት ከዚህ ሰልፍና ፍረጃ ወጥቶ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመሸጋገር በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል።
ይቺን ታላቅ አገር ወደታናሽነት ለማውረድ የሚደረግ ጥድፊያ ለከፋ ውድቀት የሚጋብዝ በመሆኑ፣ በተለይ ወጣቶች እራሳቸውን ከግጭት አምባ አርቀው በሥራና በእድገት ቀጠና ውስጥ ለመሰለፍ በአስተውሎት መራመድ እንደሚጠበቅባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ኤፍሬም ተክሌ በበኩላቸው፤ በቀጣይ 10 ዓመታት ሊተገበር የሚችል የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕቅድ በጉባኤው ለታደሙ ከፍተኛ የመንግሥት አካላትና ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ተሳታፊዎች ይፋ ያደረጉ ሲሆን፤ በዕቅዱ መሰረትም ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ወጣቶች በመጪዎቹ 10 ዓመታት በአዲሱ የሥራ ዕቅድ ፈጠራ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/2012
ሶሎሞን በየነ