P• መንግሥት ማንኛውም ሀሳብ ወደ አዳራሽ ገብቶ ውይይትና ክርክር እንዲደረግበት የያዘውን መስመር ይቀጥላል፤
• ህግን የማስከበር እና የዜጎችን ደህንነት የማረጋገጡም ሥራ ይጠናከራል
አዲስ አበባ፡- አብሮነትን የሚሸረሽሩ የቂም በቀል፣ የቁርሾና የጥፋት ሴራዎች አሁንም ድረስ አለመቆማቸውንና መንግሥት ማንኛውም ሀሳብ ወደ አዳራሽ ገብቶ ውይይትና ክርክር እንዲደረግበት የያዘውን መስመር ከማስቀጠሉ ጎን ለጎን ህግን የማስከበር እና የዜጎችን ደህንነት የማረጋገጡን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ተባለ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትናንት መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ የዴሞክራሲና የፖለቲካ ምህዳርን በማስፋት ሥራዎች እንዲተገበሩ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም አሁን ድረስ ሥርዓት አልበኝነትና በጫካ ህግ የመተዳደር አዝማሚያዎች እየተስተዋሉ ነው በዚህ ምክንያት በለውጡ ሂደት የሞት፣ መፈናቀል፣ የግጭትና የሰላም እጦት መስተዋሉን ተናግረዋል፡፡
በየጊዜው በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉ ትንኮሳዎች የመንግሥትን ሆደ ሰፊነት እየተፈታተኑትና ትእግስቱን የደካማነት ማሳያ አድርጎ የማሳየት አዝማሚያዎች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም መንግሥት በማሰር፣ በማሰቃየትና በመግደል ተግባር ውስጥ ገብቶ ተቀባይነቱን እንዲነጠቅ ለማድረግ የተጠነሰሰ ሴራ ነው ብለዋል፡፡
ከሰሞኑ በኦሮሚያ፣ድሬዳዋና ሀረር አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት እስካሁን የ78 ዜጎች ህይወት ማለፉን የገለፁት አቶ ንጉሱ በአካል ጉዳት፣ በመፈናቀልና በንብረት ላይ የደረሰው ጥፋት ምን ያህል እንደሆነ እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በወንጀል የተሳተፉ 409 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንደሚገኙበትም በመግለጫው ተጠቅሷል።
ህግን ከማስከበርና ተጠያቂነትን ከማስፈን አንፃር የሰሞኑን ሳይጨምር ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ መሰል ግጭቶች ቆስቋሾችን ጨምሮ 3 ሺህ 221 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው 2 ሺህ ያህሉ ጉዳያቸው በህግ እየታየ እንደሆነም አቶ ንጉሱ ተናግረዋል፡፡
ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ግጭቱ እንዳይሰፋ እና ከዚህ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ በቁጥጥር ስር የማዋል ሥራ በመንግሥት የተሰራ ሲሆን ለተጎጂ ወገኖች የእለት ደራሽ እርዳታ በመንግሥት፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና በህብረተሰቡ እየተደረገ እንደሚገኝም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
በየትኛውም ደረጃ በማንኛውም ኃላፊነት ላይ ያለ ግለሰብ ከተጠያቂነት አይድንም ያሉት አቶ ንጉሱ ከአክቲቪስት ጃዋር መሀመድ ጋር በተያያዘ ያለውን ሁኔታ ለማወቅና ለመፈተሽ ኃላፊነት በተሰጠው የመንግሥት መዋቅር ጉዳዩ እንደሚታይ ገልፀዋል፡፡
ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች በሀገሪቱ ከነበረው ሥርዓት ጋር ተያይዞ ትግል ለማድረግ ተቋቁመው የነበረ ቢሆንም ከአላማቸው ውጪ የመንግሥትን ሥራ ሲሰሩ እንደሚስተዋል፤ ይህንንም መንግሥት በሆደ ሰፊነት የያዘውና የማስተካከያ እርምጃ የሚወስድበትም ነው ተብሏል በመግለጫው፡፡
ከወጣቶች የሥራ እድል ጋር በተያያዘ መንግሥት ዳቦ የሚበላባቸውን ተቋማት እየገነባ ባለበት ወቅት ዳቦ እየተበላባቸው ያሉትን ማውደም የሥራ አጡን ቁጥር የሚጨምሩ መሆናቸውን በመገንዘብ መንግሥት ለወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ የሰጠውን ትኩረት መጠቀም ይገባልም ተብሏል፡፡
ሰላምን ለማስከበር እና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ብሎም ሰሞኑን በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ ከዚህ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የፀጥታ አካላት፣ ምሁራንና ወጣቶች ላደረጉት ርብርብ መንግሥት ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/2012
ድልነሳ ምንውየለት