አዳማ ከሰሞንኛ የሰላም እጦት ችግሯ የተላቀቀች ፣ ነዋሪዎቿም ወደ እለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው የገቡ ቢሆንም፣ ባለፈው ሳምንት የነበረው ድባብ ግን ሙሉ በሙሉ ተመልሷል ለማለት አያስደፍርም፡፡
‹‹እባብ ያየ፣..›› እንዲሉ የአዳማን እንቅስቃሴ፣ ሰላም አጥተው መሸሸጊያነቷን ሽተው ለሚከትሙ ዜጎች መጠለያነቷን፣ የስብሰባና የንግድ ማዕከልነቷን በእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው የለመዱ ህዝቦች ድንገት ተፈጥሮ ብዙ ባጎደለባቸው ነዋሪዎቿ ዘንድ ከአሁን አሁን ምን ይፈጠራል የሚል ስጋት እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱም አዳማ ሰሞኑን በተፈጠረው ችግር ለሶስት ቀናት የንግድ እንቅስቃሴዎቿ፣ የስራና ሌሎች ተቋሞቿ፣ መንገዶቿና አጠቃላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክንውኖቿ ተዘግተው ቆይተዋል፡፡ በርካታ ንብረት ወድሞባታል፣ የሰው ልጅ የአካልና ሕይወት ጥፋት ደርሶባታል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ 157 ሰዎች ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ 16 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ አንድ ቤት ሲቃጠል፣ 10 ቤቶች ፈራርሰዋል፤ 15 ተሸከርካሪዎች ሲቃጠሉ 14 ደግሞ መስታወታቸው ተሰባብሯል፤ 34 የግል ተቋማት ቢሮዎች ተጎድተዋል፡፡
ችግሩ የተፈጠረ ቀን ጠዋት በሰላም ወደሥራ ቢገቡም ረፋድ ላይ ቢሯቸው ባሉበት ወቅት በከተማዋ ረብሻ መፈጠሩን ሲሰሙ መደናገጣቸውን የሚገልጹት በከተማዋ የ01 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጀምበሩ ሰንበታ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ አዳማ መገለጫዎቿ ሰዎች በሰላም ወጥተው የሚገቡባት፣ ሰላማዊ የንግድና የሥራ እንቅስቃሴ የሚከናወኑባት፣ ሰዎች ተዛዝነውና ተደጋግፈው የሚኖሩባት መሆኗ ነው፡፡ በእለቱ ግን የተፈጠረውን ረብሻ ተከትሎ ሙሉ የከተማዋ እንቅስቃሴ ከመስተጓጎሉም ባለፈ ንብረት ሲወድም፣ የሰው ህይወት ሲጠፋ ማየት እጅጉን የሚያሳዝን ሁነት ነበር፡፡
ቀድሞ በአዳማ የተለያዩ ሀሳቦችና ተቃውሞዎች በሰላማዊ መንገድ ተሰምተው የሚጠናቀቁበት ሁኔታ የተለመደ ቢሆንም፤ የሰሞኑ ሁነት መልኩን ቀይሮ የመጣ፣ የዘርና የሃይማኖት ገጽታን እንዲላበስ የተደረገ፣ እጅጉን አስፈሪና የባሰ ጉዳት የሚያስከትል ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን በህዝቡና በጸጥታ ሃይሉ ትብብር ሊበርድ፤ ከተማዋም ወደመረጋጋት ልትመለስ ችላለች፡፡ ይሁን እንጂ ከነበረውና ከተፈጠረው ጥፋት አኳያ አሁንም
ህዝቡ ውስጥ ከአሁን አሁን ምን ሊፈጠር ይችላል በሚል ፍርሃትና ስጋት አለ፡፡ በመሆኑም ይህ ክስተት ዳግም እንዳይፈጠር፣ አዳማም እንደ ቀድሞው ሰላማዊ የሥራና የመኖሪያ ስፍራ እንድትሆን መንግሥት ጥበቃውን በማጠናከር የህዝቡን ደህንነት ማስጠበቅ፣ የህብረተሰቡንም ችግር ማዳመጥና ማቀራረብ፣ ህዝቡም የነበረ ህብረቱን ተጠቅሞ የራሱን ሰላም በራሱ የማስጠበቅ ድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡
በከተማዋ የ01 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ተዘራሽ ተበጀ በበኩላቸው እንደሚሉት፣ ተፈጥሮ የነበረው ችግር የሚያስፈራ፣ የተፈጸመው ተግባርም የሚያሳዝን ነው፡፡ ይህ ሁነት በህዝቡና በጸጥታ ሃይሉ የጋራ ጥረት በአጭሩ ባይገታ ኖሮ የባሰ ችግር የሚያስከትል ነበር፡፡ ሆኖም መንግሥት ከሃይል ይልቅ በሰላማዊ መንገድ እንዲረጋጋ ያደረገበት አግባብም የሚያስመሰግነው፣ ህዝቡም ሰላሙ እንዲሰፍን ያደረገው ጥረት ለሰላሙ ያለው ቀናኢነት መስካሪ ነው፡፡
ሰላም ከሚጠፋ አምባገነን መንግሥት ዝንታለም ቢገዛኝ እመርጣለሁ የሚሉት ደግሞ በከተማዋ ኬላ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ተሾመ ባጫ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ ሰሞኑን የተፈጠረው ችግር በከተማዋ ነዋሪ ጠባሳ ጥሎ ያለፈ፣ የሰላም ዋጋ በምንም ሊተካ እንደማይችል ያሳየ ነው፡፡ አሁንም ችግሩ ተዳፈነ እንጂ ሙሉ በሙሉ መፍትሄ ያላገኘ በመሆኑ መንግሥትም ሆነ የከተማዋ ነዋሪ ለሰላሙ በትኩረት መስራት ይገባዋል፡፡
ማለዳ ወደሥራ ሲሄዱ የተወሰኑ ቄሮዎች ግድያን እንቃወማለን የሚል ድምጽ በሰላማዊ መንገድ ሲያሰሙ ማድመጣቸውን፣ ሥራ ገብተው ጥቂት እንደቆዩ ግን ጉዳዩ ወደግጭት ተቀይሮ ሁኔታዎች መባባሳቸውንና መንገዶች ጭምር ተዘግተው ወላጆችም ወደትምህርት ቤት የሄዱ ልጆችን ለመውሰድ መቸገራቸውን የሚናገሩት ደግሞ የ11 ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ማክዳ ሁሴን ናቸው፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ አዳማ የኢትዮጵያ መገለጫ የሆነች ሕብረ ብሔራዊትና የሃይማኖት ብዝሃነትን አክብራ የኖረች ከተማ ናት፡፡ አሁን በከተማዋ የተፈጠረው ሁነትም የትኛውንም እምነትና ብሄር የማይወክል ነው፡፡
የአደማ ከተማ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አምሳሉ አብዲሳ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ቀደም ሲል ከተማዋ የማትገለጽበትና ሰሞኑን የተፈጠረው ተግባር እጅጉን የሚያሳዝንና የሚያሳፍርም ነው፡፡ ምክንያቱም የጥፋት ኃይሎች በእለቱ የነበረውን የወጣቶች ሰላማዊ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ሂደት ጠልፈው ስለተጠቀሙበት ንብረት ወድሟል፣ የሰው ህይወትም አልፏል፡፡ አሁን ላይ በህዝቡና በጸጥታ ኃይሉ ትብብር ከተማዋ ወደመረጋጋት የመጣች ቢሆንም፣ ከተፈጠረው ችግር አንጻር አሁንም በህዝቡ ዘንድ ስጋት አለ፡፡
የከተማ አስተዳደሩም ስጋቱን በመገንዘብ በህዝቦች መካከል እርቅና መተማመንን ለመፍጠር የሰላም መድረኮችን እያካሄደ ሲሆን፣ አጥፊዎችን ተጠያቂ ከማድረግ አኳያም እስካሁን 98 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው የማጣራት ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ አቶ አምሳሉ ገልፀዋል፡፡ ሆኖም የከተማዋ ሰላም በከተማ አስተዳደሩ የጥፋት ኃይሎችን ነቅቶ መጠበቅና ለሰላም ዘብ መቆም ይኖርበታል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/2012
ወንድወሰን ሽመልስ