አዲስ አበባ፡- የስደተኞችን አያያዝ ለማሻሻል ዓለም አቀፍ ትብብር ወሳኝ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ትናንት በአዲስ አበባ በተጀመረው የኢጋድ አባል ሀገራት የስደተኞች አያያዝ በሚመክር የጋራ ጉባዔ ላይ እንደገለፁት፤ ስደተኞችን ተቀብለው በሚያስተናግዱ ሀገራት ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቋቋም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ወሳኝ ነው፡፡
የስደተኞችን ችግር ለመቅረፍ ቋሚ የልማት ሥራዎች ላይ ተሳታፊ ማድረግና ከሚኖሩበት አካባቢ ማህበረሰብ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዲፈጥሩ መስራት ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ኢትዮጵያ ልዩ ትኩረት በመስጠት በስደተኞች አያያዝ ላይ ህጎችን በማሻሻልና ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የበኩሏን በጎ ሚና በመወጣት ላይ እንደምትገኝ ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ መሆኗን ጠቁመው ወደፊትም ለስደተኞቹ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
የሰላም ሚኒስቴር ከተባበሩት መግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽንና ከዴንማርክ ኤምባሲ ጋር በትብብር ባዘጋጀውና ትኩረቱን ለስደተኞች በሚደረገው ድጋፍ ላይ ባደረገው ጉባኤ፤ “አካባቢያዊ መፍትሔ ስደተኞችንና ተቀባይ ማህበረሰቦችን ማካተት” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ መሆኑን፤ ስደተኝነትን ከምንጩ ለማድረቅ ምን መደረግ አለበት በሚሉና ስደተኞችን በሚያስተናግዱ ሀገራት ላይ በሚደርሰው ጫና ዙሪያ መሰራት በሚገባቸው ሥራዎች ላይ ያተኮረ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘይኑ ጀማል ተናግረዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው፤ ስደተኞችን በመኖሪያ አካባቢያቸው የልማት ሥራዎች ላይ ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረው፤ ኢትዮጵያ ስትራቴጂ በመንደፍ ስደተኞችን ተቀብላ እንደ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን እያቀረበች መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ንግግር ያረጉት የአፍሪካ ህብረት የጤናና ማህበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር ወይዘሮ ፋቲክ አልዋን በበኩላቸው፤ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የስደተኞችን ችግር ለመቅረፍ በጋራ መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡ የአፍሪካ ሀገራት የስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ ለስደት መንስዔ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መስራት የሚገባ መሆኑ ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡
በስደተኞች ዙሪያ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ዓለም አቀፍ አጋር አካላትና ተቋማትንና ስምንት የኢጋድ አባል ሀገራት ተሳታፊ ያደረገው ጉባዔ በታህሳስ ወር ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የስደተኞች ፎረም ግብዓት ለመሰብሰብ የሚረዳ መሆኑም ተነግሯል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/2012
ተገኝ ብሩ