አዲስ አበባ፡- መንግሥት በተያዘው በጀት ዓመት በተለያየ ዘርፎች ለሦስት ሚሊዮን ወጣቶችና ሴቶች የሥራ እድል ለመፍጠር በቂ ዝግጅት ማድረጉን የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ መንግሥት ለ20 ሚሊዮን ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ለነደፈው የ10 ዓመት የስትራቴጂ ዕቅድ ትግበራ ከማስተር ፋውንዴሽን የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር አዲስ የአጋርነት ስምምነት ይፋ ተደርጓል፡፡
የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር ዶክተር ኤፍሬም ተክሌ በኢትዮጵያ መንግሥትና በማስተር ፋውንዴሽን በተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት መካከል በራዲሰን ብሉ ሆቴል ትናንት በተከናወነው አዲስ የአጋርነት ስምምነት የይፋ ሥነ ስርዓት ላይ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ለሦስት ሚሊዮን ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በቂ ዝግጅት በማድረግ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
ባለፉት ሦስት ወራት መነቃቃት ከመፍጠር ጀምሮ ሥራውን ለመምራትም የተለያዩ አካላት ያካተተና በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የሚመራ የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንቨስትመንት መሪ ኮሚቴ እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ካውንስል ምክር ቤትም ተቋቁሟል፡፡ ኮሚሽኑ የፌዴራል መንግሥትና ክልሎች እጅና ጓንት ሆነው እንዲሰሩ የማስተባበር ሚናውን በመወጣት ላይ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
የሥራ ዕድሎቹ በግብርና፣በአምራች ኢንዱስትሪ(ማኑፋክቸሪንግ)፣በቱሪዝምና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን የጠቆሙት ዶክተር ኤፍሬም፣የዘመኑ የግብርና ሥራ ለማከናወን ግብርና ትልቁን ድርሻ መያዙንም ጠቁመዋል፡፡በየዘርፎቹ የሚፈጠረው የሥራ ዘርፍን ጨምሮ እያንዳንዱ ክልል ሚናውን እንዲወጣ የሚያስችል ወጥ የሆነ ዕቅድ መነደፉንም ገልጸዋል፡፡ሥራውን መደገፍ የሚችሉ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትን በማሳተፍ ሀብት የማሰባሰብ ሥራን ለማከናወን እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያና በማስተር ፋውንዴሽን መካከል የተከናወነው አዲስ የአጋርነት ስምምነትም ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ዕድሜያቸው ለሥራ ለደረሰ 20 ሚሊዮን ዜጎች ሥራ ለመፍጠር ለነደፋቸው ስትራቴጂ ዕቅድ ትግበራ ከፍተኛ እገዛ እንዳለው የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፣ የአጋርነት ስምምነቱ ‹ያንግ አፍሪካ ዎርክስ› በሚል ፕሮጀክት አማካኝነት እንደሚከናወንም አስታውቀዋል፡፡
ለፕሮጀክቱም ሦስት ሚሊዮን ዶላር በጀት መመደቡንና ገንዘቡ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በሚሰሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት አማካኝነት ጥቅም ላይ እንዲውል እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሪታ ፎይ በበኩላቸው እንደገለጹት ‹ያንግ አፍሪካ ዎርክስ›ፕሮጀክት ዋና ተግባሩና ተልዕኮው ወጣቱ በሥራ ብቻ ሳይሆን በተለያየ ጉዳይ ላይ ክህሎት እንዲኖረው ማስቻልና ባገኘው ክህሎትም ኑሮውን ቀይሮ የተሻለ ዜጋ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ፋውንዴሽኑ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለመስራት የተነሳሳውም ኢትዮጵያ የወጣቶች ሀገር በመሆኗና መንግሥትም ለዜጎቹ ሥራ ለመፍጠር ተነሳሽነቱ ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20/2012
ለምለም መንግሥቱ