የኦ.ኤም.ኤን ሥራ አስኪያጅ እና አክቲቪስት አቶ ጀዋር መሃመድ “ጠባቂዎቼ በሌሊት የጥበቃ ሥራቸውን አቋርጠው እንዲወጡ ታዘዋል” ብለው ያስተላለፉትን መልዕክት ተከትሎ የተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎችን እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በአንዳንድ አካባቢዎች ለዜጎች ህይወት መጥፋት፣ ለአካል መጉደል፣ ለንብረት ውድመት ብሎም ለመፈናቀል ምክንያት የሆኑ ጥቃቶች ተፈጽመዋል፡፡ በአንፃሩ በሌሎች አካባቢዎች ሰልፈኞቹ ያለአንዳች እንከን ተቃውሟቸውንና ሀሳባቸውን ገልጸው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል፡፡ ችግር ሳይከሰት በሰላማዊ ሰልፍ ህዝቡ ቅሬታውንና ተቃውሞውን ካሰማባቸው አካባቢዎች መካከል የምዕራብ አርሲ ዞኗ አዳባ ወረዳ ትጠቀሳለች፡፡
በአዳባ የተካሄደው ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፉ ያለ አንዳች ችግር የተጠናቀቀው እንደሌሎች አካባቢዎች አጋጣሚውን ተጠቅመው የንጹሃንን ደም ሊያፈሱና ንብረት ሊያወድሙ የሚፈልጉ አካላት ስላልነበሩ አይደለም፡፡ ህዝብ ሰልፍ ከመውጣቱ አስቀድሞ ተወያይቶበት፤ ጥቃት እንዳይፈጸም ጥንቃቄ ለማድረግና እኩይ ተግባር ፈጻሚዎችን በጋራ ለመከላከል ሕዝባዊ ውይይት አድርጎ ነው፡፡
የአዳባ ወረዳ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ወይዘሮ ፎዚያ መሃመድ እንደተናገሩት፣ ረቡዕ ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በወረዳዋ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያካሂድ ነበር፡፡ ወጣቶች ሰላማዊ ሰልፍ ሲያካሂዱ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና የሃይማኖት እንዲሁም ቄሮዎች ሰላማዊ ሰልፉን እንደምቹ አጋጣሚ ተጠቅመው የብሄርና የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር ለሚሞክሩ ኃይሎች ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር በውይይታቸው ሀሳብ ተለዋውጠውበታል፡፡
ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፉ ለግማሽ ቀን ከተካሄደ በኋላ በወረዳው አስተዳደር አስተባባሪነት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና ቄሮዎች በጋራ በመሆን ሰላማዊ ሰልፍ ከወጣው ህዝብ ጋር ሕዝባዊ ውይይት ማድረጋቸው በቀጣይ ቀን በወረዳው የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ያለአንዳች ችግር እንዲከናወን ሚናው የጎላ ነበር፡፡
እንደ ወይዘሮ ፎዚያ ገለጻ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተለይም ለአዳባ ቅርብ በሆኑ ዶዶላና ኮፈሌ ሰላማዊ ሰልፉን እንደምቹ ሁኔታ በመጠቀም የብሄርና የሃይማኖት መልክ ያላቸው ግጭቶች ተፈጥረዋል፤ ይሁን እንጂ አዳባ ላይ መሰል ችግር እንዳይፈጠር የተደረገው ህዝባዊ ውይይት አቅም ሆኗል፡፡ በሕዝባዊ ውይይቱ በርካቶች የተሳተፉበት ሲሆን ግጭቶች እንዳይከሰቱ ሁሉም ቃል ገብተው ተለያይተዋል፡፡
በአዳባ የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ለመንግሥት ቅሬታ ለማሰማት እንጂ የትኛውንም ብሄርና የሃይማኖት ተከታይ ለማጥቃት እንዳልሆነ፤ መሰል ተግባር የሚፈጽሙ አካላት የሚኖሩ ከሆነም በጋራ ለመከላከል በውይይት መድረኩ ከስምምነት መደረሱን የሚያነሱት ወይዘሮ ፎዚያ፤ ሰላማዊ ሰልፉ ለጸረ ሰላም ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆን በጋራ ለመከላከል በውይይቱ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ችግሮች እንዳይፈጠሩ አድርጓል፡፡
እንደ ወይዘሮ ፎዚያ ማብራሪያ፤ ሕዝባዊ ውይይት በመደረጉ የአዳባን ሰላም ማስጠበቅ ከመቻሉም በላይ በአጎራባች አካባቢዎች የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ እገዛ አድርጓል፡፡ ለአብነት ያህል በአዳባ ለሁለት ቀናት የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ በሰላም ከተጠናቀቀ በኋላ የአዳባ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ወጣቶች ከአዳባ በ25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በዶዶላ ላይ የተፈጠረውን ግጭት ለማብረድ እገዛ አድርገዋል፡፡
በአዳባ ወረዳ የተደረገው ህዝባዊ ውይይት ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን በውይይትና በመነጋገር መፍታት እንደሚቻል ትልቅ ተምሳሌት ነው ያሉት ወይዘሮ ፎዚያ ዜጎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ደስታቸውንም ሆነ ቅሬታቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ሊገልጹ ቢችሉም ሁኔታውን ለጥፋት ሊያውሉ የሚችሉ ኃይሎችን ማምከን እንደሚቻል አስገንዝበዋል፡፡
የምዕራብ አርሲ ዞን የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አወል ሀሰን በበኩላቸው፤ በዞኑ በሚገኙ በ15ቱም ወረዳዎች ከሰላማዊ ሰልፉ አስቀድሞ ሕዝባዊ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ ከ15ቱ ወረዳዎች ውስጥ በ12ቱ ያለ አንዳች ችግር ህዝቡ ድምጹን አሰምቶ ወደ ቤቱ ተመልሷል፡፡
በ12ቱ ወረዳዎች ግን የታየው መልካም ተግባር ህዝባዊ ውይይቶች ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል እንደመፍትሄ ሊወሰድ እንደሚገባ አሳይተዋል፡፡ በሶስቱ ወረዳዎች ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የማይፈልጉ ኃይሎች የብሄርና የሃይማኖት መልክ አስይዘው ግጭት እንዲቀሰቀስ አድርገዋል፡፡
በ15ቱ ወረዳዎች የተካሄዱ ሕዝባዊ ውይይቶች ችግሮችን ለማምከን ትልቅ አቅም ሆነዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በአጠቃላይ ሕዝባዊ ውይይት ምን ያህል እድል አግኝቷል? ስንል ለምናነሳው ጥያቄ ምላሹ ‹‹ተነፍጓል ነው››፡፡
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ዓለምአቀፍ ጉዳዮች መምህርና የታሪክ ተመራማሪ ዶክተር አብዱ መሀመድ አሊ እንደሚሉት፤ በሀገሪቱ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ አብዛኞቹ ችግሮች በህዝባዊ ውይይቶች ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን ህዝባዊ ውይይቶች ጥቅም ላይ እየዋሉ ባለመሆናቸው ችግሮችን መከላከል የሚቻሉ አለመግባባቶች ዋጋ እያስከፈሉ ነው፡፡
ከለውጡ በኋላ ከወትሮው በተሻለ መልኩ የምሁራንና የፖለቲከኞች የውይይት መድረኮች ሲዘጋጁ እንደነበር የሚያነሱት ዶክተር አብዱ፤ ውይይቶቹ ግን ህዝቡን በሚፈለገው ልክ ያሳተፉ አለመሆናቸውን ያነሳሉ፡፡ የውይይት መድረኮቹ ወደታች ወርደው ሕዝባዊ ሆነው እድል ቢያገኙ በርካታ ጠቀሜታዎች ያስገኛሉ ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር አብዱ ማብራሪያ፤ ወደታች ተወርዶ በቀበሌ፣ በወረዳ ወይም በዞን ደረጃ በክፍለ ከተማ ጭምር ሕዝባዊ ውይይቶች ተከናውነው የወቅቱን ችግሮች በሚገባ ለመለየት ይቻላል፡፡ መፍትሄውስ ምንድን ነው? የሚል ሕዝባዊ ውይይት ሊዘጋጅ ይገባል ሲሉ መክረዋል፡፡ ህዝብም የችግሮች መፍትሄ ሳይሆን ለድጋፍ ብቻ የሚፈልግ የፖለቲካ ባህል በመኖሩ ህዝባዊ ውይይቶች ተዘንግተዋል ይላሉ፡፡
በሀገሪቱ በየአቅጣጫው የሚከሰቱትን ችግሮች ሁሉ ለመንግሥት ትቶ አብዛኛው ተመልካች ሆኖ የሚዘልቅበት ሁኔታ ማብቃት አለበት፤ ለዚህም መንግሥት ሁሉም ዜጋ የሚሳተፍባቸውን ህዝባዊ የውይይት መድረኮች ማዘጋጀትና ህዝቡን የመፍትሄ አካል ማድረግ ይገባል የአስተያየት ሰጪዎቹ መቋጫ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20/2012
መላኩ ኤሮሴ