አዲስ አበባ:- በውጭ ሀገር ሆነው በተቃውሞ የራሳቸውን አቋም ሲያራምዱ የነበሩና በመንግሥት ጥሪ ሀገር ውስጥ ለገቡ ግለሰቦች ለደህንነታቸው ሲባል እየተደረገላቸው ያለው ልዩ ጥበቃ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ውጭ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ በአዋጁ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር ልዩ ጥበቃ የሚያደርግላቸው ሀገርንና ህዝብን ይጠቅማሉ ተብለው በመንግሥት ለተሾሙ የሥራ ኃላፊዎች፣ ከውጭ ሀገር ለሚመጡ መሪዎች፣ የክብር እንግዶች መሆኑን አመልክቷል፡፡
በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የህግ ባለሙያ ኮማንደር ፋሲል አሻግሬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ አክቲቪስት ጀዋር መሐመድን ጨምሮ መንግሥት ባደረገው ጥሪ መሰረት ሀገር ውስጥ ሆነው ለሀገር የሚጠቅም ሥራ ለመስራት ተስማምተው የገቡ እንደመሆናቸው ለደህንነታቸው ሲባል ይደረግላቸው የነበረው ጥበቃ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ አፈጻጸም ውጭ ነው፣ በህግ የተጣለ ግዴታም የለም፣ በመንግሥት ውሳኔ የተፈጸመ ነው፡፡
አክቲቪስት ጀዋር ሀገር ውስጥ ሲገቡ ደጋፊ እንዳላቸው ሁሉ ተቃዋሚም ሊኖራቸው ይችላል በሚል ለደህንነታቸው ሲባል ጥበቃ እንደተደረገላቸው የጠቆሙት ኮማደር ፋሲል በሀገሪቷ ውስጥ ለእርሳቸው ስጋት የሚሆን ነገር የለም ተብሎ ከታሰበም ጥበቃው በማንኛውም ጊዜ ሊነሳ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
በኮሚሽኑ ጥበቃ የሚደረግላቸው አካላት በማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 7/20/2004 ዓ.ም በአንቀጽ አምስት ንዑስ አንቀጽ ዘጠኝ ላይ በግልጽ መስፈሩን የጠቆሙት ኮማደር ፋሲል፣ መንግሥት ሀገርንና ህዝብን ይጠቅማሉ ብሎ ኃላፊዎችን ሲሾም ኃላፊነቱ ቀጥታ የፖሊስ ኮሚሽን በመውሰድ ጥበቃ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
በአዋጁ መሰረት የውጭ ሀገር መሪዎች፣ የክብር እንግዶች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲቆዩ ጥበቃ ይደረግላቸዋል። የጥበቃው አስፈላጊነትም በእነርሱ ላይ የሚደርሰው ጉዳት ለሀገር ደህንነትና ገጽታ ግንባታም የሚኖረውን አሉታዊ ተጽእኖ ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ኮማንደሩ አስረድተዋል።አፈጻጸሙም ተገቢውን ስልጠና ባገኙ አካላት እንደሚከናወንና የሚመደበው ኃይል ቁጥርም እንደሚለያይ ገልጸዋል።
ጥበቃው የሚነሳበትንም ሲያስረዱ ጥበቃ ለግለሰብ ሳይሆን ለቦታ በመሆኑ ኃላፊው የቦታ ለውጥ ቢያደርግም ጠበቃው ይኖራል ብለዋል። ኃላፊው በጡረታ ተገልሎም ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚችልም ጠቁመው ጥበቃው የሚደረግለት ግለሰቡ በአዋጁ መሰረት በሚያቀርበው ጥያቄና እንደአስፈላጊነቱ እንደሚቀየር አስታውቀዋል።
በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ረዳት ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ መአዛ ኃይማኖት ወርቁ የጥበቃ ዋና ተግባር ወንጀልን መከላከል መሆኑን ጠቁመው፣ፖሊስም ሲቋቋም ወንጀልን ቀድሞ መከላከል፣ የተፈጸመ ወንጀል ካለም መርምሮ ለፍርድ ማቅረብ በመሆኑ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ተግባሩን ነው የተወጣው ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20/2012
ለምለም መንግሥቱ