አዲስ አበባ፡- የብሔራዊ አንድ ዋሽ በሁለተኛው ዙር ፕሮግራሙ ለ6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሕዝብ ንጹህ የመጠጥ የውሃ አቅርቦት ተደራሽ እንደሚያደርግ የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ይፋ አደረገ፡፡
ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ትናንት በካፒታል ሆቴል ከባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄደው ውይይት ላይ እንደገለጹት፤ ሁለተኛው ዙር ብሔራዊ 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን በገጠር፣ አንድ ሚሊዮን በከተማ እና አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሕዝብ ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ተደራሽ ይሆናል፡፡ ለፕሮግራሙ ማስፈጸሚያም 569 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ከመንግሥትና ከአጋር ድርጅቶች መገኘቱንም አመልክተዋል፡፡
ሁለተኛው ዙር የአንድ ዋሽ ፕሮግራም 70 በመቶው በገጠራማው የሀገሪቱ ክፍል፤ 30 በመቶው ደግሞ በከተሞች አካባቢ የሚገኘው የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንደሚሆን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣በከፍተኛ ሁኔታ ለተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭ የሆኑ እና በድርቅና በምግብ እጥረት የሚጠቁ አካባቢዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
ፕሮግራሙ ውሃ ወለድ የሆኑ በሽታዎችን በመከላከል፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የሴቶችን የትምህርት ማቋረጥ በመቀነስና አቅም በማጎልበት እንዲሁም የጾታ እኩልነትን በማረጋገጥ በኩል ዘርፈ ብዙ ተግባራት እንደሚያከናውን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
ሁለተኛው ዙር የአንድ ዋሽ ፕሮግራም እ.ኤ.አ ከ2019 እስከ 2024 ድረስ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡
በመጀመሪያው ምዕራፍ 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሕዝብ የገጠር እና ዜሮ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በከተማ ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የንጽህና አጠባባቅና ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት(ሳኒቴሽንና ሐይጂን) አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረጉ፣10224 የንጽህና መጠበቂያና የመጸዳጃ ተቋማትን በትምህርት ቤቶችና በጤና ተቋማት በመገንባት አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡
የውሃ መስኖና ኢነርጂ የጤና፣የትምህርት እና የገንዘብ ሚኒስቴር መስሪያቤቶች በቅንጅት የሚተገብሩት የአንድ ዋሽ ፕሮግራም ለክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም ለተጠያቂነት አመቺ እንዲሆን ከተጀመሩት አሰራሮች አንዱ እቅድ፣ አንድ በጀትና አንድ ሪፖርት በሚል ከመንግሥት አሰራር ስርዓት ጋር በተጣጣመ መልኩ የሚተገበር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20/2012
ሙሐመድ ሁሴን