አዲስ አበባ፡- የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የከተሞች ዕድገት ፈጣን፣ ምቹና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን የባለ ድርሻ አካላትን ቅንጅትና ተሳትፎ ያማከለውን አዲሱን የከተሞች አጀንዳ ትብብር ይፋ አደረገ፡፡
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ ሙሐመድ ትናንት በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተከናወነው የይፋ ሥነሥርዓት ላይ እንዳመለከቱት አዲሱ የከተሞች አጀንዳ ትብብር ምቹና ዘለቄታ ያላቸው ከተሞችን ለመገንባትና ለመቆጣጠር እንዲሁም በከተሞች ዕድገት ዙሪያ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በትብብርና በቅንጅት እንዲሰሩ ለማስቻል የሚረዳ ነው፡፡
ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው የሰዎች ፍልሰት እየጨመረና በአምስት ነጥብ አራት በመቶ እያደገ መምጣቱን የጠቆሙት ሚኒስትሯ ከተሞችን በአግባቡ በመቆጣጠር መምራት ካልተቻለ የልማት እድገትን ለማረጋገጥ አዳጋች እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡
እንደሀገር በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ሊሰሩ የታሰቡ ጉዳዮችን በጥናትና በዕቅድ በመምራት ተቋማትና ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ የጋራ የውይይት መድረክ ማዘጋጀት አስፈልጓል፡፡ በዚህም ለጋሽ ድርጅቶች፣ ኤንባሲዎች መንግሥታዊ ተቋማት፣ የጥናትና ምርምር ማዕከሎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ሌሎችንም በማካተት ሊሰራ መታቀዱን አመልክተዋል፡፡
‹‹ዩ ኤን ሀቢታት›› ፣የዓለም ባንክ እና ሌሎች አጋሮች ፕሮግራሙን የመደገፍ ፍላጎት እንዳለቸው የተናገሩት ሚኒስትሯ ድጋፍና ትብብሩን በአንድ ቋት አስገብቶ መተርጎም እና በአግባቡ መምራት በማስፈለጉ ጠንካራ አደረጃጀት ለመፍጠር ታስቧል ብለዋል፡፡
እንደሚኒስትሯ ገለጻ ሚኒስቴሩ ስለ ከተማ መሬት አያያዝ፣ ስለከተማ ፕላን፣ስለቤቶች ግንባታና ስለመሰረተ ልማት ስለስራ አጥነት ወዘተ ጥናት አካሂዷል፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ ለሚፈልሱት ወጣቶች ሥራ ለመፍጠርና በቤት ልማት ላይ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ በጥናቱ ተለይቷል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20/2012
ኢያሱ መሰለ