– ሁሉን ነገር በግጭት ለመፍታት የሚያስቡትን ወጣቱ በቃችሁ ሊላቸው ይገባል
– ግድቡ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ የሚሠራ ነው
– ምርጫውን ለማድረግ በቂ ዝግጅት አለ
አዲስ አበባ፡- ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ለህዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ባለፈው መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም ባቀረቡት የመክፈቻ ንግግር ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ማብራሪያ ሰጡ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ትናንት ሲካሄድ የምክር ቤቱ አባላት በፕሬዚዳንቷ ንግግር ላይ እንዲያብራሩላቸው የፈለጉትን ጥያቄዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል። ከአባላቱ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል በተለያዩ አካባ ቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማቆም መንግሥት በበጀት ዓመቱ ስለሚወስዳቸው ማስተካከያዎች ማብራሪያ እየተጠየቀበት ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ በሰጡት ማብራሪያ ባለፉት 45 ዓመታት በጦርነት በርካታ ወገኖቻችንን ማጣታችንና፤ ለአካል ጉዳትም የተዳረጉ እንዳሉ በማንሳት ሁሉም ቦታ ላይ ግጭት የሚፈጥሩት አንድ አይነት ሰዎች ናቸው ብለዋል።
ይህም ከባለፈው አለመማር ነው፤ ሁሉ ነገር በግጭት ነው የሚፈታው ብለው የሚያምኑ አሉ። እነሱ ያስገድላሉ እንጂ አይሞቱም ወጣቱ ይህን ተገንዝቦ እነዚህን ሰዎች በቃችሁ ሊላቸው ይገባል ብለዋል።
የግጭትን መሠረታዊ አመጣጥና አፈታት መገንዘብ ጠቃሚ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግጭትን የምንገነዘብበትና የምንፈታበት መንገድ ችግር ያለበት ነው። ግጭትን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት አይቻልም። በተቀናጀ ወይም ባልተቀናጀ መንገድ ችግር ሊፈጠር ይችላል፤ ዋናው ጉዳይ የሕግ አስከባሪውን አቅም መፍጠርና ግጭት ከተፈጠረም ማረም መቻል እንደሆነ አብራርተዋል።
በአማራና በትግራይ ክልል መካከል የሚየታየውን መካረር አስመልክቶም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩም ክልሎቹ ሲሰዳደቡ ቢውሉ ሁለቱ ህዝቦች ለዘላለም አይለያዩም። ሁለቱ ክልሎች በስሜት ተነሳስተው ከተጋጩም በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ተፈጥሮ ሁላችንም በታሪኩ እንዳፈርነው ይሆናል ብለዋል።
“እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ የትግራይን ክልል የሚመሩ ጥቂት ግለሰቦች የትግራይን ህዝብ የልማት ችግር ለመፍታት የሚፈልጉ ናቸው። በመሐል ያሉ ናቸው ችግር የሚፈጥሩት እነዚህን መለየት ያስፈልጋል” ሲሉም አክለዋል። አሁን ባለው የፖለቲካ ትኩሳት ድህነትን ሳናሸንፍና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳይኖረን ክላሽ አይጠቅመንም ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መክረዋል።
ቅማንትንና አማራን በሚመለከትም የሚበጀው ቆም ብሎ መወያየት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከአማራ ክልል መንግሥትና ህዝብ በላይ ለቅማንት ህዝብ የሚቀርብ አንድም አካል የለም። ይኸን ጉዳይ በተመለከተ በአብዛኛው ከስምምነት መደረሱንና በሦስት ቀበሌዎችም ያለውን ችግርም በሠላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚቻልም ጠቁመዋል። ሁለቱም አካላት ውስጣቸውን አይተው መፍታት ይገባቸዋል። በመካከል እሳት እያቀጣጠሉ የሚሞቁ ግን መኖር አይችሉም ከዚህ ይልቅ ለዘላቂ ሠላም መሥራት ይገባል ብለዋል።
ዶክተር አብይ፤ በአሁን ዘመን መንገድ በመዝጋት አይደለም ድንበር በመዝጋት እንኳን ጥቅምን ማረጋገጥ አይቻልም። መንገድ መዝጋት የኋላ ቀርና የብሽሽቅ ፖለቲካ ውጤት ነው። መንግሥትን ለመቃወምም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመሳደብ አዳራሽ የተሰበሰበን ሰው አዳራሽ ገብቶ መረበሽም አግባብ አይደለም።
ሰው በሠላማዊ መንገድ እንዲቃወም ካለማመድነው የኋላ ኋላ ወደ አመጽና ግጭት መግባቱ አይቀርም። የአማራንና የኦሮሞን፣ የአማራንና የትግራይን ህዝብ ለይቶ ማስቆም በማይቻልበት ሁኔታ መንገድ መዝጋት ተገቢነት የሌለው የኋላቀር ፖለቲካ አካሄድ ውጤት በመሆኑ ከዚህ መውጣት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
አሁን ያለው እሳት የመለኮስ ጉዳይ እየበረደ ይሄዳል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥት እርምጃ መውሰድ አቅቶት ሳይሆን እርምጃ መውሰዱ ችግሩን ስለማይፈታው በሆደ ሰፊነት ይዞት ነው ብለዋል። ዜጎችም ይህን ተገንዝበው ለሠላም መትጋት አለባቸው። ችግሩ በኢትዮጵያና በህዝቦቿ ላይ የከፋ ችግር የሚያመጣ ከሆነ ግን መንግሥት እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነው። አብዛኛው ለሚያባሉን ሰዎች በባዮሎጂም መልስ ስላለው በቀጣይ ይበርዳል ሲሉም ተስፋ ሰጥተዋል።
በምክር ቤቱ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበላቸው ሌላው ጥያቄ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምን፣ በህዳሴ ግድብ ላይ ግብጽ እያነሳቸው ያለው ጥያቄና የምርጫ መካሄድን የተመለከተ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ መገናኛ ብዙሃንን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ “የውጭ አገር ዜጋ የሆናችሁ የሚዲያ ባለቤቶች፣ የኢትዮጵያ ፓስፖርት የሌላችሁ የሚዲያ ባለቤቶች፤ ስትፈልጉና ሠላም ሲሆን እዚህ ተጫውታችሁ እኛ ችግር ውስጥ ስንገባ ጥላችሁ የምትሄዱበት ሁለት አገር ያላችሁ ሰዎች ትግስት እያደረግን ያለነው አውዱን ለማስፋት ነው። ይሁንና በማንኛውም ሰዓት በኢትዮጵያ ሠላምና ህልውና ላይ ከመጣችሁ አማረኛም ሆነ ኦሮምኛ ብትናገሩም እርምጃ መውሰዳችን የማይቀር መሆኑን በጥንቃቄ መገንዘብ አስፈላጊ ይሆናል።
ሁለት ቤት መጫወት አይቻልም፤ እኛ የምንሄድበት አገር የለንም። አገራችን ይሄ ስለሆነ ሠላም እንፈልጋለን። ተቀያሪ ያላችሁ ሰዎች በነፃነት ሠላማችን፣ ልማታችንንና ዴሞክራሲያችንን ካገዛችሁ እሰዬው በደስታ፤ ከዚያ ውጭ ግን ለመነገጃ የምትጠቀሙበት ከሆነ በዚህ ሁኔታ በነፃነትና በዴሞክራሲ ስም የሚቀለድ እንዳልሆነ ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የህዳሴ ግድብን በተመለከተም ግድቡ የኢትዮጵያን ጥቅምና ክብር በሚያስጠብቅ መልኩ የሚሠራ ፕሮጀክት ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ የግብጽን ህዝብ የመጉዳት ፍላጎት የለውም፤ ከሀብቱ በፍትሃዊነት መጠቀም ነው የሚፈልገው ብለዋል። የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የጀመሩ መሪዎች ሥራን ምርጥ ሥራ ስለሆነ፤ መጨረስ አለብን። በእኛና በግብጽ መካከል የተለየ የሚያነጋግረን አጀንዳ የለም።
የግብጽ መንግሥትና ህዝብ ማተኮር ያለበት ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአረንጓዴ ልማት በቀጥታ ማገዝ ነው። በህዳሴ ግድብ ላይ እየተነሳ ላለው ማንኛውም አይነት ጥያቄ ችግር ፈጣሪዎቹ እኛ ነን፤ ባስቀመጥነው ልክ ብንጨርሰው ኖሮ አጀንዳ አይሆንም ነበር በማለትም ስለመዘግየቱ ቁጭታቸውን ተናግረዋል።
ዶክተር አብይ፤ ምርጫውን አሁን አንችልም በሚቀጥለው እናድርግ ካልን ብዙ ችግር አለው። አሁን ላይ ምርጫውን ማድረግ በብዙ መንገድ ጥቅም አለው። ምርጫውን ለማድረግም በቂ ዝግጅት አለ። ለምርጫ ቦርድ የተመደበው ሀብት ባለፉት አምስት ምርጫዎች ከተመደበው የበለጠ ነው።
የምርጫ ቦርድ አደረጃጀት በንፅፅር ከምንጊዜውም በተሻለ ነፃ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ አሸንፎ መምራት ብቻ ሳይሆን ተሸንፎ በሠላማዊ መንገድ ሥልጣን ማስረከብም ትልቅ ታሪክ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ምርጫን ተከትሎ የሚፈጠሩ ግጭቶች ምን እንደሚያስከትሉ ከምርጫ 97 ተረድቷል፤ ስለዚህ ምርጫን ተከትሎ የሚነሳን ግጭት አይፈልግም፤ ቢፈጠርም እንዴት እንደሚያልፈው ያውቃል ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች አሸንፈው መንግሥት በመሆን ብቻ የሚያምኑ ከሆነ የፖለቲካን ሙሉ ቅርፅ አያሳይም፤ መሸነፍንም መለማመድ ያስፈልጋል። በቤተሰብ፣ በጓደኛ በማህበር የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት አያዋጣም፤ ለኢህአዴግ ጭምር ሰብሰብ ማለት ነው የሚበጀው ሲሉ ከመለሱ በኋላ መንግሥትንና ፓርቲን እንዲሁም ፓርቲንና ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ማየት ተገቢ አለመሆኑንም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ