አዲስ አበባ:- ግንባታው ለተጠናቀቀው የአዋሽ ኮምቦልቻ የባቡር መስመር ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ሥራን በተመለከተ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይልና የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽ መግባባት አልቻሉም።
የኢትዮጵያ ምድር ባብር ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚና የባቡር ኔትወርክ ዘርፍ ሃላፊ አቶ የኋላሸት ጀመረ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታው መዘግየት ሃላፊነቱን መቶ በመቶ መውሰድ ያለበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ነው።
አቶ የኋላሸት እንደሚሉትም፤ ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡርና ለአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር ዝርጋታ ኤሌክትሪክ ያቀረበው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ነው። አሠራሩ በዘፈቀደ የተወሰደ ሳይሆን ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠው ሥራ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ሃይለማርያም ደሳልኝ አማካኝነት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የሃይል አቅርቦቱን ማቅረብ እንዳለበት በደብዳቤ ታዟል።
ይህ ደብዳቤ እስካሁንም አልተሻረም። በዚህ መሰረት ለባቡር መስመሩ የሚያስፈልገውን ሃይል አሳውቀው የመስመር ዝርጋታ መረጣ ቢያካሂዱም እንዲሁም ለወሰን ማስከበር ካሳ የሚሆን ብድር ተገኝቶ በጋራ ለመክፈል ስምምነት ቢፈረምም ሥራው አልተጀመረም።
ሥራውን ከዛሬ ነገ ይጀመራል ብለን እየጠበቅን ባለንበት ወቅት ሥራው ከዜሮ ተጀምሮ ተጨማሪ 18 ወራት ይፈጃል ማለታቸው ተገቢ አይደለም ያሉት አቶ የኋላሸት፤ ኤሌክትሪኩ ባለመቅረቡ አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር የወጣበት ፕሮጀክት ያለምንም ሥራ ተቀምጧል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የኮሚኒ ኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን በዚሁ ዙሪያ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ምላሽ፤ ተቋማቸው ተበድሮ ለኮርፖሬሽኑ የኤሌክትሪክ መስመር አይዘረጋም ብለ ዋል።
“ክፍያ ፈጽመው ውል ሳንገባ ኤሌክትሪክ እንደማንዘረጋ አሳውቀናል” ያሉት አቶ ሞገስ፤ ተቋማቸው ለአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር የኤሌክትሪክ አቅርቦቱን በራሱ ወጪ አለመሥራቱን አስታውሰው፤ ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ግን በተቋማቸው ወጪ መስመር መዘርጋቱ ስህተት መሆኑን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በአዋጅ የተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት ክፍያ ፈፅሞ እንዲሠራ ነው ያሉት አቶ ሞገስ፤ ለአዋሽ ኮምቦልቻ የባቡር መስመር ፕሮጀክትም ኮርፖሬሽኑ ክፍያ ሲፈፀም ብቻ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ነው ያስረዱት።
ፕሮጀክቱ የሚገኝበት የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አማካሪ አቶ ደሳለኝ አስራደ በዚህ ዙሪያ በሰጡት አስተያየትም፤ ፕሮጀክቱ የፌዴራል መንግሥት እንደመሆኑና ተቋማቱ የፌዴራል በመሆናቸው ሁለቱ ተቋማት መግባባት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ግንባታው አልቆ አገልግሎት እንድናገኝ እንፈልጋለን ያሉት አቶ ደሳለኝ፤ ኮምቦልቻ፣ ደብረብርሃን እና በክልሉ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ደረቅ ወደቦች የባቡር መስመሩን ለመጠቀም እየተጠባበቁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በነሐሴ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ዕትሙ በዚህ ፕሮጀክት ዙሪያ በሰራው ዘገባ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ክፍያ አልፈፀመም በሚል ምክንያት ሥራው እንዳልተጀመረና፤ ክፍያው ቢፈፀምም ኤሌክትሪክ ለማቅርብ በአማካይ 18 ወራት እንደሚያስፈልግ መዘገባችን ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2012
አጎናፍር ገዛኽኝ