አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ከሚመረተው ንፁህ ውሃ 40 በመቶው አካባቢ እንደሚባክን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የውሃ ልማት ከሚሽነር ዶክተር በሻህ ሞገሴ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ በአገሪቱ ከሚመረተው ንፁህ ውሃ በዝቅተኛ 14 በመቶ በከፍተኛው እስከ 45 በመቶው ይባክናል። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን መጀመሪያ ከሚመረተው ውሃ በአማካይ ከ39 እስከ 40 በመቶ እንደሚባክን ታውቋል።
ይህም ከሚመረተው ሁለት ሊትር ውሃ አንዱን እንደመድፋት ማለት ነው። ባደጉት አገራት ከሚመረተው ንፁህ ውሃ የሚባክነው 3 በመቶው ብቻ ነው። ከዚህ አንፃር ከ30 ሚሊዮን ውሃ በላይ ህዝብ የንፁህ ውሃ መጠጥ በማያገኝባት አገራችን ከፍተኛ የውሃ ሀብት እየባከነ እንደሆነ ያሳያል።
እንደኮሚሽነሩ፤ ማብራሪያ የሚባክነውን ውሃ እንዲቀንስ ከመሥራት ይልቅ ትኩረት የሚደረገው አዲስ ግንባታ ማካሄድ ነው። ይህ ደግሞ ከፍተኛ የሀብት ብክነት እያስከተለ ነው። በመሆኑም አዲስ ለመገንባት የሚሰጠውን ትኩረት ያህል የነባሩን ውሃ አጠቃቀም ከብክነት ለማዳን መሠራት ይኖርበታል።
ውሃን ከብክነት ለማዳን የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት፣ የሚገነቡ የውሃ ልማቶችን ለጥገና ምቹ አድርጎ መገንባት፣ ዩኒቨርሲቲዎች አዲስ ግንባታ ለማካሄድ ብቻ ሳይሆን ጥገና የሚያደርጉ ባለሙያዎችን ለማፍራት መሥራትና የውሃ ተቋማት ብክነትን ለመቀነስ እሳት የማጥፋት አካሄድን ከመከተል ይልቅ የውሃ ጥገና ሥርዓት መዘርጋት እንዳለባቸውም አመላክተዋል።
ኮሚሽነሩ የብክነቱ ምክንያት የቧንቧ መሰበር፣ የውሃ ማጠራቀሚያ ማፍሰስ፣ ሥርቆት፣ ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ የመንገድ ዳር ያሉ አትክልቶችና ሌሎች በርካታ ምክንያቶች መሆናቸውን በመጥቀስ ይህንን ለመቀነስ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህም አንፃር የ22 ከተሞች የውሃ ብክነትን ለማሻሻል እየተሠራ ሲሆን የ44 ከተሞችን የውሃ ብክነት ለማሻሻል ዝግጅት እየተደረገ ነው። ከመረጃ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመቅረፍም በመላ አገሪቱ የ200 ሺ የውሃ ተቋማት መረጃ ተሰብስቧል።
ይህም መረጃ ከታህሣሥ እስከ የካቲት ባለው ጊዜ ይፋ ይደረጋል። የውሃ ታሪፍ ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብክነት ስለሚታይም ይህን ለማስተካከል ዝቅተኛውን ህብረተሰብ የማይጎዳ የታሪፍ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውሃ ቴክኖሎጂ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር፣ አሰልጣኝና ተመራማሪ አቶ ዘውዱ ሰይፉ፤ በአገራችን በሚመረተው ንፁህ ውሃ ከፍተኛ ብክነት እንዳለ በዶክተር ባሻህ የተነሳውን ሃሳብ ያጠናክራሉ።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በአዲስ አበባ የውሃ ብክነት 45 በመቶ የደረሰ ሲሆን በአጠቃላይ የውሃ ብክነት ለአገራችን የውሃ አገልግሎቶች ትልቁ ፈተና ሆኗል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ብክነትን ዜሮ ያደረገ አገር ባይኖርም በኢትዮጵያ የሚባክነው ግን ከፍተኛ ነው።
እሳቸው እንደሚሉት ለብክነቱ ትልቁ መንስኤ የውሃ መረጃ ችግር ነው። የውሃ ተቋማት የሚያመርቱትንና ለህብረተሰቡ የሚያደርሱትንም በትክክል አያውቁትም። የውሃ ግድቦችና ጉድጓዶች ትላልቅ መለኪያ ሜትሮች የሏቸውም።
አብዛኞቹ የውሃ መጠናቸውን የሚያውቁት ማጠራቀሚያዎቻቸው ሲሞሉ ስለሆነ ከሚያመርቱት ውሃ ምን ያህል እንደባከነና ጥቅም ላይ እንደዋለ አያውቁትም። የሚመረተው ውሃ መረጃ የተተነተነ ካለመሆኑም በላይ የዘረጓቸውን ቧንቧዎችና መስመሮች እንዲሁም ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ መስመሮች ላይ የተሟላ መረጃ የላቸውም።
ከውሃ አገልግሎት እስከ ተጠቃሚዎች የውሃ መስመሮች ማስረግ፣ የባንቧ መቀደድ፣ የማጠራቀሚያና የማምረቻ ጥራት መጓደል፣ የቆጣሪ ጥራት ማጣትና ብልሽት፣ የውሃ መስመሮች ማርጀት፣ የግንባታና የዕቃዎች ጥራት ችግር ለብክነቱ ዋና ዋና መንስኤ ናቸው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከቆጣሪ በፊት መስመር በመቀጠል፣ ቆጣሪ በማበላሸትና በመሳሰሉት መንገድ የውሃ ሥርቆት መደረጉ ሌላው የውሃ ብክነት ምንጭ ነው። በተለይም በአዲስ አበባ ከሚባክነው ውሃ 15 በመቶው በሥርቆት የሚባክን መሆኑም አስደንጋጭ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ዘውዱ እየባከነ ያለውን ውሃ መፍትሔ ለመስጠት የውሃ አገልግሎቶች ከሚ ያመርቱት ውሃ ምን ያህሉ ለህብረተሰቡ ጥቅም እየዋለ እንደሆነ በትክክል ለማወቅ የሚያስችል ከማምረቻው እስከ ተጠቃሚው ያለውን መረጃ የሚያውቁበት የውሃ መለኪያ መትከል፣ ከመለኪያው የሚደርሰውን መረጃ በማደራጀት መተንተን፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የውሃ አገልግሎት መሣሪያዎች ጥራት እንዲኖራቸው ቁጥጥር ማድርግ፣ ጥራት ያለው ግንባታና መሣሪያ መጠቀም፣ ሥርቆትን ለማቆም ግንዛቤ መፍጠርና የውሃ ተቋማትን በብዛት ለመገንባት ከማስብ ይልቅ ብክነትን ለመቆጣጠር የሚያስችል መዋቅር ዘርግቶ መሥራት እንደሚገባ መክረዋል።
የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ታመነ ኃይሉ፤ በበኩላቸው አንድ ሜትር ኪዮብ ውሃ ለማምረት ከፍተኛ ወጪ ይወጣል። ንፁህ ውሃ ለማቅረብ መንግሥትም ይደጉማል። ይሁንና እየተከሰተ ያለው ከፍተኛ ብክነት አገርን እየጎዳ ከመሆኑም በላይ ለህብረተሰቡ የውሃ አገልግሎት ለማዳረስም እንዳይቻል አድርጓል ብለዋል።
ለውሃ ብክነት ዋናው ችግር የውሃ ተቋማት መሪዎችና ባለሙያዎች ብቃትና ግንዛቤ አለመኖር፣ የውሃ መስመሮች በአግባቡ አለመዘርጋትና ግንዛቤ ኖሮት የሚሠራና የበቃ ተቋምና ባለሙያ በዘርፉ አለመፈጠር ናቸው። በአዲስ አበባ ያለው ብክነት በለገዳዲ ግድብ ያለውን የውሃ መጠን ያህል አምርቶ ያለጥቅም እንደማፍሰስ ይቆጠራል። ይህን ችግር ለመግታትም አዲስ ከምንገነባው የውሃ ተቋም በዘለለ ያሉትን በመጠገን ለመጠቀም ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ንፁህ ውሃን ለማምረት እንደየቦታውና የውሃ አቅርቦቱ ቢለያይም ለውሃ አቅርቦት ለአገልግሎቱ ሥራ ማስኪያጅያ የሚወጣውን ሳያካትት በነፍስ ወከፍ ለአንድ ነዋሪ ከ100 እስከ 700 ዶላር ይወጣል። ለምሳሌም ያህል ከ340 ሺ በላይ ህዝብ ላላት ድሬዳዋ ከተማ የውሃ አቅርቦትን ተደራሽነት ከ62 ወደ 90 በመቶ ለማሳደግ 900 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2012
አጎናፍር ገዛኽኝ