የመደመር እሳቤ አቅምን አሟጦ ብክነትን ቀንሶ በመጠቀም የጋራ ግቦች እውን የሚደረጉበት፣ የሀገር ህልውና የሚረጋገጥበት የንቃት መንገድ መሆኑን ዶክተር አብይ አህመድ ሰሞኑን ይፋ ባደረጉት መደመር መጽሐፍ ላይ ተብራርቷል።
ዋነኛ ዓላማውም ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ድሎችን ጠብቆ ማስፋት፣ የተሠሩ ስህተቶችን ማረም እንዲሁም የመጪውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጎት ማሳካት መሆኑም ተገልፀዋል።
‹‹መደመር›› ከችግር ትንተና አንፃር ሀገር በቀል መሆኑንና ከመፍትሔ ፍለጋ አንፃር ደግሞ ከአገር ውስጥም ከውጭም ተቀምሮ እንደተሰነደ ዶክተር አብይ በመጽሐፋቸው ይነግሩናል።
ብያኔውን ሲያመለክቱም የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎችን ጨምሮ ሁሉንም ግላዊና ማህበረሰባዊ የህይወት ዘይቤን የሚነካ እሳቤ ሲሆን፤ አላባዎቹ ኢትዮጵያ ልትሄድበትና ልትደርስበት የሚገቡ መንገዶችና መዳረሻዎች ናቸው ይላሉ።
ባለፉት አራት ዓመታት የተቀጣጠለው ሀገራዊ ለውጥ ፍንትው አድርጎ ያሳየው ዘላቂና አፋጣኝ መፍትሔ የሚፈልጉ አገራዊ ተግዳሮቶች ለእሳቤው መዳበር ገፊ ምክንያቶች መሆናቸውንም ጸሐፊው ያስረዳሉ።
በፌዴራል ጥናት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሠሩት የሕግ አማካሪና ጠበቃው አቶ ዝናቡ ይርጋ፤ ‹‹መደመር›› በባህሪው ርዕዮት አለመሆኑን፤ ከጽንሰ ሃሳቡ መረዳት የሚቻለው የካፒታሊስትነት ባህሪ ያለው፤ ነፃ ገበያን የሚያበረታታ፣ ለህዝባዊ ተሳትፎ ዕድል የሚሰጥ፣ ገበያ መር አስተሳሰብ ያለበት ነው ባይ ናቸው።
አብዮታዊ ዴሞክራሲም ምሉዕ ርዕዮት እንዳልሆነና የማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮት መሆኑን ያስታውሱና፤ እነማርክስ ካፒታሊዝምን ትተው ወደ ሶሻሊዝም ሥርዓት እንደመሻገሪያ ጀምረውት የነበረ የተሟላ ርዕዮት ያልነበረው ጽንሰ ሃሳብ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ወደ ውህድ የሚሻገረው ፓርቲ አካታች የካፒታሊስት ርዕዮት እንደሚያቀነቅንና ህዝብና መንግሥት ተሳትፎ እንዲኖራቸው እንደሚያስችልም ይናገራሉ።
በሕግና በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዲሁም በልማት ጥናት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሠሩት አቶ ዘሪሁን ጋሻውም፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲና መደመር አይነፃፀሩም ይላሉ።
አብዮታዊ ዴሞክራሲ፤ ኢህአዴግ ከጊዜ በኋላ እመራበታለሁ ብሎ ያስቀመጠው ርዕዮተ ዓለም ሲሆን፤ በአመራሮች ደረጃም ቃሉን ከመጠቀም በዘለለ አስተሳሰቡን በበቂ ሁኔታ ግንዛቤ እንዳልተያዘበትም ይናገራሉ። መርሆዎቹ በተለያየ መንገድ መቀመጡን ይጠቁሙና፤ እንደ አገር የተደራጀ ሰነድ እንደሌለውና በዓለም አቀፍ ደረጃም ርዕዮተ ዓለሙ እንደማይታወቅ ይገልፃሉ። ከመደመር አተያይ ጋር አነፃፅሮ ለማስቀመጥ አይቻልም ባይ ናቸው።
መደመር ዕሳቤ እንጂ ፍልስፍና ተደርጎ መታየት አይችልም የሚሉት አቶ ዘሪሁን፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ፅንሰ ሃሳብ ሲሆን፤ በዕራሳቸው መንገድ ለአገሪቱ አዋጪነቱን ካለፉበትና ካለው ነባራዊ ሁኔታ ተነስተው የፈጠሩት እንጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ የማይታወቅ መሆኑን ይጠቁማሉ። በኃላፊነታቸው ደረጃ ያመጡት ሃሳብ ተቋማዊ አድርጎ ለማስቀጠል ማስፈፀሚያ ዕቅድ እንደሚያስፈልገው ያመለክታሉ።
መደመር በርዕዮት ዓለም ደረጃ ተግዳሮት አይኖረውም የሚሉት አቶ ዝናቡ ደግሞ፤ የነፃ ገበያ ሥርዓትን ይከተል የነበረው ኢህአዴግም ምሉዕነት ባይኖረውም ጀምሮት እንደነበረ ያመለክታሉ።
ከ27 ዓመታት በላይ ጎራዎች ተለይተዋል የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ አክራሪ፣ ጠላትና ወዳጅ ኃይሎች የመደመር ትልቅ ተግዳሮት ናቸው። አስተሳሰባቸው ለዝቦ አብሮ መኖር፣ መረዳዳትና ኢትዮጵያዊነት ትርጉም እንዳለው በመገንዘብ ከጠባብነትና አግላይነት አስተሳሰብ የተሻለ መሆኑ እስኪታመን የመደመር ተግዳሮት ይሆናል።
ህወሓት በውህድ አስተሳሰቡ ሃሳቡን አለማመኑ ሌላው ፈተና ይሆናል የሚሉት አቶ ዝናቡ፤ ቋንቋ መር የነበረው የክልል አወቃቀሩ ሌላው እንቅፋት ሊሆን እንደሚችልም ያመለክታሉ።
‹‹መደመር›› ጸሐፊው መሰባሰብንና ውህደትን ለመግለፅ የተጠቀሙበት ሃሳብ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ያመለክቱና፤ ከመበታተን ይልቅ፤ ኃይልን፣ እውቀትንና ጉልበትን አሰባስቦ መንቀሳቀስ የተሻለ ዕድል ለመፍጠር ያስችላል የሚል መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳብ መያዙን አቶ ዘሪሁን ይጠቅሳሉ።
አጠቃላይ ለውጡ የሚመራበት ሰነድም ሆነ አቅጣጫ እንደሌለው ከተለያየ አቅጣጫ የሚነሳውን ትችት በተወሰነ መልኩ ሊመልስ ይችላል ብለው ያመጡት ሃሳብ ከሆነ ሃሳባቸውን በግልፅ ማስቀመጥ አለበት ይሉና፤ ሃሳባቸውን በበቂ ሁኔታ አለመገለፁ ከተለያዩ አካላት ትችት ሊገጥመው እንደሚችልም ይናገራሉ።
አቶ ዘሪሁን አንዳንዶች መደመርን የለውጡ ደጋፊ መሆን፤ አለመደመርን ደግሞ ተቃዋሚ በማድረግ በአረዳድ ያለው ክፍተትም ሌላው ሳንካ ሊሆን እንደሚችል በመግለፅም፤ በክልልም ደረጃ የህወሓት ኃይል ሃሳቡን ያለመቀበሉ አንድ ችግር ሊሆን እንደሚችል ይጠቅሳሉ። ሃሳቡ የተለየ መሆኑም ሌላው ፈተና እንደሚሆን ይናገራሉ። በጠቅላይ ሚኒስትሩና በአመራር ደረጃ ያሉ የተለያዩ አካላት የሚቀነቀነው ፍፁም የተለያየ ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋትም አላቸው።
አስተሳሰቡ በትክክል ከተተገበረ ዜጎችን አብሮ ያኖራል፣ እንዲደጋገፉ ዕድል ይፈጥራል፣ የእኛ የሚል አስተሳሰብ ያጎለብታል፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የውህድ ቤተሰቦች ውጤት መሆኑን እውቅና ይሰጣል ባይ ናቸው አቶ ዝናቡ።
ተገልለው ለቆዩ አምስቱ ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ኢትዮጵያዊ እውቅና ይሰጣል፣ በመወለድ ሳይሆን በዕውቀት ለመምራት የሚያስችል አቋም የያዘ በመሆኑ ሌላው ስኬት ይሆናል ይላሉ። ‹‹ቁርሾዎችን በብሔራዊ እርቅ እፈታለሁ›› የሚለው ከልብ ወደ ተግባር ከተገባም ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ድርሻ ይኖረዋል። የሚያኮርፍ ኃይልን ቁጥርም ሊቀንስ እንደሚችልም ያመለክታሉ።
ሐሳቡ የግለሰብ ነው ወይስ የአገር? የሚለው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም የሚሉት አቶ ዘሪሁን፤ መጽሐፉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስም መውጣቱ የአገር ሃሳብ ሊያደርገው አይችልም ይላሉ። በቀደመው ተሞክሮ ሰነድ በግለሰቦቹ ስም እንደማይወጣ ያስታውሱና፤ ሃሳቡ የድርጅቱ እንደሆነና የመንግሥት ፖሊሲ አካል ተደርጎም እንደሚወሰድ ይገልፃሉ።
ሐሳቡ ኢትዮጵያን ወደሚፈለገው ደረጃ ያሸጋግራታል? የሚለው ጥያቄ ያልተፈተነና የቀጣይ ጊዜ ፈተና ሊሆን ይችላል ብለው ሰግተዋል። ሃሳቡ እንደአገር የነበሩ እጥረቶች የሚሻሻሉበትን ሁኔታ መጠቆሙ መልካም መሆኑን ይጠቅሱና፤ አገሪቱን የሚጠቅም እንዲሆን ሁሉም አምኖበት ለተፈፃሚነቱ መረባረብ ይኖርበታል ባይ ናቸው።
ዶክተር አብይ በመጽሐፋቸው መደምደሚያ፤ በመጽሑፉ የተካተቱ ሃሳቦችን ጨምሮ ቀለል ባለ መልኩ የመደመር መሰረታዊ ሃሳቦችና ሌሎች ሃሳቦችን ያካተተ መጽሐፍ በቅርቡ ለአንባቢ ይቀርባል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2012
ዘላለም ግዛው