አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እያስገነባ ያለው ሃምሳ ሁለት ወለል የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ እ.ኤ.አ በህዳር ወር 2020 ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የቻይና ስቴትኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡
በኮርፖሬሽኑ የሕንፃ ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ፋንግ ዜን ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት ግንባታው ከተጀመረ አራት ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ህንፃ የማጠናቀቂያ ሥራዎች ካለቁ በኋላ እ.ኤ.አ በ2020 ይጠናቀቃል፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ በአራት ዓመታት የሕንፃ ግንባታው ሂደት ልዩ ልዩ የስትራክቸር ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እየሄደ በመሆኑ በቀረው አንድ ዓመት ውስጥ የመስታወት ማቀፊያ ፍሬም ተገጥሞ የሕንፃውን የውጭ ክፍል መስታወት የማልበስ ሥራ ይሠራል፡፡
ለዚህ የማጠናቀቂያ ሥራም ከየሥራ ክፍሉ የተውጣጣ ቡድን ተቋቁሞ ቻይና ድረስ በመሄድ የዕቃዎች መረጣና በሕንፃው ላይ ሊተገበሩ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን የመለየት ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡
በየሥራ ክፍሉ የመስመር ዝርጋታ (ኬብል ዳታ ኢንስታሌሽን) ሥራዎችና በሕንፃው የውስጠኛ ክፍል የማስዋብ (ኢኒቴሪየር ዲዛይን) ሥራዎች እንደሚከናወኑም ሥራ አስኪያጁ አያይዘው ገልፀዋል።
ሕንፃው ባረፈበት ምድረግቢ ውስጥ የመሰረተ ልማት ግንባታና ግቢ የማስዋብ ሥራዎችም በተመሳሳይ እንደሚሠሩ ጠቁመው ከምድር በታች ባሉት የህንፃው አራት ወለሎች ውስጥም የግድግዳ ማጠናቀቂያ፣ የጂፕሰምና የቀለም ሥራዎች እንደሚሠሩም ሥራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል፡፡
206 ሜትር ርዝማኔ ያለውና ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚው ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ መሆኑ የተነገረለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ በ164 ሺ 429 ስኩዌር ሜትር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን ለግንባታው 298 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ወጪ እንደተደረገ ከኮርፖሬሽኑ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2012
አስናቀ ፀጋዬ