አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያን ጨምሮ በኬንያና ኡጋንዳ በቻይናና በአገራቱ ትብብር በየዓመቱ የሚካሄደው የቻይና-አፍሪካ ኢንዱስትሪ አውደ ርዕይ ለሁለተኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ትኩረቱን ያደረገው ሁለተኛው የኢትዮ-አፍሪካ ኢንዱስትሪ ትብብር አውደ ርዕይ ከአስራ አምስት ግዛቶች ከመጡ የቻይና ልዑካን ቡድንና የኢትዮጵያ የቻይና የዘርፉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት በትናንትናው ዕለት ሲከፈት የአውደ ርዕዩ ተባባሪ አዘጋጅ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መላኩ እዘዘው (ኢንጅነር) እንዳሉት በአውደ ርዕዩ የሚሳተፉት በኢንዱስትሪያል ምህንድስና፣ በኃይል ማምረቻ ቁሳቁሶች፣ በግብርና ምርቶች ቅንብርና በተሽከርካሪ ምርት ኢንዱስትሪዎች ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ዘርፎቹ በኢትዮጵያ ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራባቸው ነው ሆኖም አውደ ርዕዩ ከትልልቅና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ካላቸው የቻይና አምራቾች ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል በመሆኑ አምራች ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ያለው የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ትብብር በየጊዜው እየተጠናከረ መምጣቱንና ለሁለቱ አገራት ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ያመላከቱት ፕሬዚዳንቱ አውደ ርዕዩ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከምትገኘው ቻይና በርካታ ልምዶችን ለመጋራት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ተወካይና የአምባሳደሩ አማካሪ ሚስተር ዥያ ቲያን በበኩላቸው፤ በወንድማማችነትና በወዳጅነት ለታጀበው የቻይናና የኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ግንኙነትና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ዋነኛው መሠረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“ለዚህም ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ ቻይናን በጎበኙበት ወቅት ሁለቱ አገራት የተፈራረሙት የአራት ቢሊየን ዶላር የኢኮኖሚ ትብብር ትልቅ ማሳያ በማድረግ አንስተዋል፤ወደፊትም ግንኙነቱ ከዚህም የበለጠ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ከተጀመረ ሁለተኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የቻይና-አፍሪካ የኢንዱስትሪ ትብብር አውደ ርዕይ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ፈርጀ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ትብብር አጠናክራ ለመቀጠል ባላት ቁርጠኝነት የተነሳ ተግባራዊ የተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ከጥቅምት 11 እስከ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄደውና በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ ከአርባ በላይ የቻይና ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2012
ይበል ካሳ