– ንብረታቸው ለወደመባቸው ባለሀብቶች ካሳ አልተከፈለም
አሶሳ፡- አምና ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ ችግር የእርሻ ሥራን በማስተጓጎሉ የተፈጠረውን ክፍተት ለማካካስ በተቀናጀ መንገድ የመስኖ እርሻ ሥራ መጀመሩን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገለፀ። ንብረታቸው ለወደመባቸው ባለሀብቶች ድጋፍም ሆነ ካሳ አለመደረጉም ተጠቁሟል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙሳ አህመድ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ በመተከል ዞን አካባቢ ዘር መዝራት በሚጀመርበት ወቅት ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ ችግር ሥራውን አስተጓጉሎታል። አብዛኞቹ ባለሀብቶች ወደ እርሻ ሥራቸው በጊዜ ስላልገቡም ሊያመርቱት የሚገባው ምርት አልተመረተም።
አካባቢው ከክልሉ አጠቃላይ ምርት 50 በመቶ የሚመረትበት ቢሆንም ችግሩ ከተፈጠረበት ዳንጉር ወረዳ ሰው ለቆ በመውጣቱና መሬቱ በጊዜ ባለመታረሱ ምርት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ሥጋታቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ከመስከረም 20 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በተቀናጀ መንገድ የመስኖ እርሻ መጀመሩን፣ 67 ሺ ሄክታር መሬት ይታረሳል ተብሎ እንደሚገመት፣ የመስኖ ምርታማነትን በመጨመር ከስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለማግኘት መታቀዱንም ገልፀዋል።
ኃላፊው ውሃ ገብ በሆኑ መሬቶች ባለሀብቶች ጭምር እንዲያለሙ ማድረግ ካልተቻለ የባለፈው ዘመን ምርት በሚፈለገው መጠን ላይካካስ እንደሚችል ጠቁመው፤ ዘንድሮ የመስኖ ሥራ ለክልሉ የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑን ጠንክሮ ካልተሠራ በምርት ገቢና በምግብ ፍጆታ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አመልክተዋል።
‹‹ባለሀብቶች ሙሉ ለሙሉ አልወጡም። የወጡትን የመመለስ ሥራም ተሠርቷል። በዘር ጊዜ የወጡት መተከል፣ ዳንጉርና ማንዱር ወረዳ ላይ ያሉ ናቸው›› ያሉት አቶ ሙሳ፤ መረጋጋቱንም በመመልከት አብዛኞቹ ወደ ሥራቸው መመለሳቸውን ነገር ግን ምን ያህል እንደገቡና የሚቀሩት ምን ያህል እንደሆኑ በሚመለከተው አካል ኦዲት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
አቶ ሙሳ በግብርና ሥራው የ2010 /11 ዓ.ም የመኸር እርሻ ምርት አንድ ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 888 ሺ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን መቻሉን፣ 34 ሚሊየን ኩንታል ምርት ታቅዶ 22 ሚሊየን ኩንታል መገኘቱን ፣ በመስኖ 109 ሺ ሄክታር ለመሸፈን ታቅዶ 33 ሺ ሄክታር መሸፈኑንና ዝቅተኛ አፈፃፀም መመዝገቡን፣ በሁሉም ወረዳዎች መረጃዎች የተሰበሰቡ ሲሆን፤ የካማሽ ዞን፣ የማኦ እና ኮሞ ልዩ ወረዳ በፀጥታ ምክንያት መሥራት እንዳልተቻለ አብራርተዋል።
አቶ ሙሳ የእንስሳት መድሃኒት እጥረት አጋጥሞ እንደነበረ፣ በእንስሳት ማድለብ፣ በንብ ማነብና በዓሣ እርባታ ጥሩ አፈፃፀም ቢኖርም ክልሉ ካለው ሀብት አኳያ ዕድገቱ አዝጋሚ መሆኑን ፣የማህበረሰቡ የእንስሳት አረባብ ዘዴ ኋላ ቀር መሆኑ፣ ባለሙያዎች የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ አገልግሎት በሚፈለግባቸው ልክ የማቅረብ ውስንነት፣ በአንዳንድ ወረዳዎች የገንዲ በሽታ ያሳደረው ሥጋት አፈፃፀሙን አነስተኛ ማድረጉንም ጠቅሰዋል።
በተያያዘ ዜና በክልሉ ንብረታቸው ለወደመባቸው ባለሀብቶች የተደረገላቸው ድጋፍም ሆነ ካሳ እንደሌለ የክልሉ የአካባቢ መሬት አስተዳደርና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገልጿል። በቢሮው ማስፋፊያና ማበረታቻ ዳይሬክተር የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ክትትልና ድጋፍ ባለሙያው አቶ ደረጄ አበበ አብዛኞቹ ጉዳት የደረሰባቸው ባለሀብቶች ማመልከታቸውን ተናግረዋል።
ቢሮው ይህንኑ ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ማሳወቁን፣ ኮሚሽኑም ከንግድ ባንክ፣ ከልማት ባንክና ከመድን ድርጅት ቡድን አዋቅሮ ጥናት ሲያደርግ ቢቆይም እስከአሁን ድጋፍ እንዳልተደረገላቸውና ካሳ እንዳልተከፈለ ገልፀዋል።
አቶ ደረጄ ባለሀብቶቹ የክልሉ መንግሥት ከቻለ ካሳ እንዲከፍላቸው፤ ካልሆነም ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ጠቁመው፤ የክልሉ መንግሥት ባለሀብቶቹ የደረሰባቸው ኪሳራ እንዲጣራ በሰጠው ትዕዛዝ ማጣራት ለመጀመር ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2012
ዘላለም ግዛው