አዲስ አበባ፤ በምዕራብ ኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ባለመስፋፋቱ በብዛት ወጣቱ ተምሮ ሥራ አጥ መሆኑንና ሂደቱም በእኩይ ተግባር ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ዓላማ እንዲከተሉ ማድረጉን የምዕራብ ወለጋ ዞን አስታወቀ።
የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ኤሊያስ ኡመታ በተለይ ከጋዜጣው ሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ በቅርቡ የተወሰደውን መረጃ ዋቢ በማድረግ በምዕራብ ወለጋ ብቻ የመጀመሪያ ዲግሪ እና ከዚያ በላይ ያላቸው ወጣቶች ቁጥር ከስድስት ሺህ በላይ ደርሷል።
በዚህ የተነሳ አንዳንድ ወጣቶች በእኩይ ተግባር ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ዓላማ መከተላቸውን እና የጸጥታ ችግሩ እንዲባባስ ማድረጉን ያነሱት የዞኑ አስተዳዳሪ ችግሩን ለመቅረፍ ከሰላም ማስከበር ጎን ለጎን የስራ እድሎች የሚሰፉበት አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በምዕራብ ኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ባለመስፋፋቱ ወጣቶች ተምረው ወደ ቀዬአቸው ይመለሳሉ የሚሉት አቶ ኤልያስ በዚህ የተነሳም ሥራ አጥ ተበራክቷል፤ ይህ ደግሞ ድህነት እንዲባባስ አድርጓል ብለዋል።
ብድር ወስደው በመደራጀት የሚሰሩ ወጣቶች ቢኖሩም ችግሩን ብዙ ሊቀንሰው እንዳልቻለ አቶ ኤሊያስ ጠቁመው፤ ብድር በተሟላ ሁኔታ ያለመገኘት እና የአሰራር ችግሮች እንዳሉም አብራርተዋል።በመንግሥት ተቋማት ይህንን ሁሉ ቀጥሮ ማሰራት የማይቻል መሆኑንም አመልክተዋል።
ላለፉት 10 ዓመታት ሲጠና የነበረ በገንጂ ወረዳ የሚገኝ የወርቅ ማዕድን ዘንድሮ ወደ ተግባር ስለሚገባ እስከ 10 ሺ የሚደርሱ ሥራ አጦችን እንደሚያሳትፍ በመጠቆም፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በመንግሥ ትም የተለያዩ ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል አቶ ኤሊያስ።
በህብረት ሥራ ማህበራትና በግለሰቦች የቡና ምርት፣ በአካባቢው የሚመረተውን ማንጎ እና የተለያዩ ማዕድና ትን እሴት ጨምሮ እንዲላክ በማድረግ ለአካባቢው ህብረተሰብ የተሻለ ገቢ ለመፍጠር መታቀዱን አመልክተዋል።
ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ባለመስፋፋታ ቸው አርሶ አደሩ ከምርቱ ተጠቃሚ አለመሆኑንና የመሰረተ ልማት ውስንነትና የሥራ እድል ፈጠራውም በሚፈለገው ልክ ባለመሄዱ ችግሩ መባባሱን አቶ ኤልያስ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2012
ዘላለም ግዛው