በአገሪቱ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የመሠረታዊ ሸቀጦች የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። የዋጋ ንረቱን በዘላቂነት ለመቆጣጠር የገበያ ስርዓቱን ማስተካከልና የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንደሚያስፈልግ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ፍሬዘር ጥላሁን እንደሚናገሩት፤ በአገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች የዋጋ ንረት ተፈጥሯል። በአገሪቱ ያለው የዋጋ ንረት የተፈጠረው የገበያ ስርዓቱ የተዘበራረቀ በመሆኑና የአቅርቦትና ፍላጎት ያለመጣጣም በመኖሩ ነው።
በሌላ በኩል አርቴፊሻል ገበያዎች በአገሪቱ ያለው የዋጋ ንረት እንዲባባስ ምክንያት ናቸው። በአሁን ወቅት ያለው የዶላር እጥረት ለዋጋ ንረቱ ሌላው ምክንያት ቢሆንም በአገር ውስጥ የሚመረቱና ምንም አይነት የውጭ ግብዓት የማይጠቀሙ እንደ ቲማቲም እና ሽንኩርት ምርቶች ዋጋቸው በየቀኑ መጨመሩ ግን የገበያ ስርዓቱ መበላሸት ማሳያ ነው።
በአገሪቱ የአቅርቦት ችግር፣ የምርት መቀነስ እንዲሁም የህብረተሰቡ ፍላጎት ማደግ እየታየ እንደሚገኝ የሚናገሩት አቶ ፍሬዘር፤ መንግሥት ምርት የቀነሰበት ምክንያት ምን እንደሆነ ትኩረት ሰጥቶ መከታተል እንዳለበት ይናገራሉ። ለምርት መቀነስ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት እንደ ዋና ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችልም ያመላክታሉ። በተጨማሪም ለአቅር ቦት መቀነስ ምክንያት የኢንቨስትመንትና የንግድ ፖሊሲዎች ትግበራ መፈተሽ እንዳለበት ይጠቁማሉ።
እንደ አቶ ፍሬዘር ገለፃ፤ የገበያ እንቅስቃሴው ላይ ማሻሻያዎች ይደረጉ ሲባል መንግሥት ሙሉ ለሙሉ ገበያ ውስጥ ይግባ ማለት አይደለም። በተወሰነ መልኩ ገበያው ነፃ መሆን አለበት። ምርታማነትን በሚጨምር መልኩ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በተወሰነ ደረጃ ያስፈልጋል። በአሁን ወቅት ገበያው በውስን ነጋዴዎች ቁጥጥር ስር ይገኛል። ምርቶች በየጊዜው ዋጋቸው መጨመሩ ደግሞ የገንዘብን ዋጋ እንዲቀንስ አድርጎታል።ይህንን ለመቆጣጠር ፖሊሲዎች መዘጋጀት አለባቸው። የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር አሁን ያለውን የግብይት ስርዓት መታየት አለበት።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ መላኩ እንደሚናገሩት፤ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ፍላጎትና አቅርቦቱ የተጣጣመ መሆንና ገበያው ስርዓት መያዝ አለበት። እነዚህ ነገሮች መሆን ካልቻሉ ዋጋው መረጋጋት አይችልም። ለዚህም አቅርቦት ላይ መሰራት አለበት።
ለምሳሌ የግብርና ምርት፣ የኢንዱስትሪ ምርቶች ወይም ከውጭ የሚገቡ ምርቶች አቅርቦት ላይ በስፋት መሰራት አለበት። በአገሪቱ በአሁን ወቅት በቂ አቅርቦት እያለ ገበያው ላይ አርቴፊሻል የዋጋ ንረቶች እንዲፈጠሩ ተደርጓል። አርቴፊሻል ንረቱ ከነጋዴዎች መስገብገብ ሊሆን ስለሚችል በህግ አግባብ የቁጥጥር ስርዓት መፈጠር አለበት።
የዋጋ ንረቱ በተወሰነ መጠን መረጋጋት ካቻልቻለ ለመንግሥት ፈተና እንደሚሆኑ የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ፤ በተጨማሪም የታችኛው ማህበረሰብ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ እንዲገፋ እንደሚያደርገው ያስረዳሉ። የዋጋ ማረጋጋቱ ላይ በጥልቀት እስካልተሰራ ድረስ አገሪቱን ለመምራት ከባድ እንደሚሆንም ያመለክታሉ።
ዋጋ ለማረጋጋት አቅርቦት ላይና አርቴፊሻል ንረትን መቆጣጠር ከተቻለ ለውጥ እንደሚመጣ ያስገነዝባሉ። ዋጋ ማረጋጋት ከመግዛት አቅም ጋር የሚያያዝ እንደመሆኑ የገንዘብ ዋጋ ሲቀንስ ወደ ዋጋ ንረት ሊወስድ እንደሚችል ይጠቅሳሉ። በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የገንዘብ መጠን የመቆጣጠሩ ጉዳይ መታየት እንዳለበትም ይናገራሉ።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የ2012 ዓመት የህዝብ ተወካዮች ምክርቤትና የፌዴሬሽን ምክርቤት መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት ያለው የዋጋ ንረት በተለይ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የሚጎዳ በመሆኑ የዋጋ ንረቱን የመቆጣጠር ሥራ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የዋጋ ንረቱ በዋናነት የሚስተዋለው በምግብ ሸቀጦች ላይ ስለሆነ መንግሥት የመሠረታዊ የምግብ ሸቀጦችን በበቂ መጠን ከውጭ በማስገባት የዋጋ ንረቱ ሸማቾችን እንዳይጎዳ የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ በበጀት ዓመቱ እንደሚሰራም አስገንዝበዋል።
እንደ አቶ ፍሬዘር አባባል፤ መንግሥት ገበያ ውስጥ ሲገባ በመጀመሪያ ዓይን ያወጡ የገበያ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላትን በተለይ በቤት ኪራይና በትራንስፖርት ዘርፉ የሚስተዋሉትን ለማስቆም መሆን አለበት። በመቀጠል በየቀኑ ያለውን የገበያ ሁኔታ መረጃ ለህብረተሰቡ መስጠት ይጠበቅበታል።
ወደ ውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ በተለይ የነዳጅ፣ የስንዴና መሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ድጎማውን መቀጠል አለበት። ነጋዴው የማያቀርባቸው ምርቶች ላይ መንግሥት ገዝቶ ለህብረተሰቡ በመሸጥ በተወሰነ መንገድ ገበያውን ማረጋጋት ይጠበቅበታል። መንግሥት እነዚህን ማድረግ ካልቻለ የዋጋ ንረቱ ይበልጥ ስለሚጨምር መንግሥትን ስጋት ላይ ይጥለዋል።
እንደ አቶ ተስፋዬ አባባል፤ መንግሥት ጣልቃ ሊገባ የሚችለው አምራቹን ዘርፍ በመደገፍ ነው።ድጋፍ ሲያደርግ አቅርቦቱ የማደግና የመጣጣም ነገር ያመጣል። በሌላ በኩል የመንግሥት የማስፈፀም አቅም በተለይ አርቴፊሻል ንረት ሲፈጠር ነጋዴዎችን በህግ እንዲመሩ ማድረግና የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠት አለበት። አሁን ያለው የዋጋ ንረት ለመቆጣጠርም ፓሊሲዎችን በማውጣት መስራት አለበት።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2012
መርድ ክፍሉ