• የሚዲያ ህግ ማሻሻያ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ:- በመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች መረጃ ሲጠየቁ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ የተቋማት ኃላፊዎች በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባ ተጠቆመ። የመረጃ አሰጣጥ ስርዓቱን ለማሳለጥ የሚዲያ ህጉ ላይ ማሻሻያ እየተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት በየተቋማቱ ያለው መረጃ የህዝብ ሀብት እንጂ የግለሰብ ንብረት አይደለም። በመሆኑም መረጃ ለህዝብ ጥቅም ተብሎ ሲፈለግ ወይም ህዝቡ ማወቅ እፈልጋለሁ ይሰጠኝ ሲል መረጃውን የያዙ ኃላፊዎች የመስጠት ግዴታ አለባቸው።
አቶ ዝናቡ ቱኑ እንደሚሉት የመንግሥት ተቋማት ቀዳሚ ተልእኮው ህዝብን ማገልገል፣ የህዝብን ደህንነት መጠበቅ እና የህዝብን ጥያቄ መመለስ በመሆኑ ህዝብ ለሚያቀርበው ጥያቄ ሁሉ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል።
“መረጃን ለመገናኛ ብዙኃን የመስጠት ጉዳይን በተመለከተ በተለያዩ ህጎች ላይ ተቀምጧል። ይሁን እንጂ አሁንም እዚህም እዚያም ላለመስጠት የሚደረጉ ሙከራዎች ይታያሉ። ይህ ሊቀርና ተቋማትም ከዚህ አይነቱ የተሳሳተ አሠራር መውጣት አለባቸው። ይህን የማያደርግ ኃላፊ ካለ በህጉ መሰረት ሊጠየቅ ይገባል” የሚሉት ዳይሬክተሩ ለአገር ሰላምና ደህንነት ሲባል ከሚከለከሉት መረጃዎች ውጪ ሌላውን መረጃ የሚከለክል ኃላፊ በህግ ሊጠየቅ፤ ጋዜጠኛውም እምቢ ሲባል ዝም ብሎ ሊመለስ ሳይሆን ሊከስና እምቢ ባዩን በህግ ሊያስጠይቅ፤ የሚፈልገውንም መረጃ የማግኘት መብቱን ሊያስከብር እንደሚገባም ተናግረዋል።
እንደ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ ገለፃ ጋዜጠኛው መረጃ የከለከለውን አካል በህግ እንዲጠየቅለት ማድረግ መብቱ ብቻ አይደለም፤ ይህን የማድረግ ኃላፊነትም አለበት። ይህን ሁሉም አካል በመረባረብ ሊያደርገው ይገባል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ በመረጃ የበለፀገ ማህበረሰብ መፍጠር አይቻልም። በመረጃ የበለፀገ ማህበረሰብ መገንባት ደግሞ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ግልፅ ነው፤ በመረጃ የበለፀገ ማህበረሰብ አጋዥ በመሆኑና ልማትን ለማፋጠን፤ ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን የሚጫወተው ሚና ተኪ የሌለው ነው።
መረጃ የመጠየቅ፣ የማወቅና የመጠቀም መብት የዜጎች ህገ መንግሥታዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እንጂ ሌላ ከማንም ለማንም የተሰጠ አይደለም የሚሉት አቶ ዝናቡ የሚዲያ ህጉ በሚገባ ተፈትሾ ይህንን ጉዳይ በሚገባ እንዲያሳልጥ ተደርጎና እንደገና የህግ ማእቀፍ ተዘጋጅቶለት ረቂቁ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት እንደሚገኝ፤ ቀደም ሲል የነበረው የመገናኛ ብዙኃን መረጃ የማግኘት ነፃነት ህግም እየታየና እንደገና የማሻሻል ሥራ እየተሰራበት መሆኑን፤ ተቋማትና ኃላፊዎች መረጃ እንዲሰጡ ለማድረግ የሚያስገድድ ሁኔታ እንዲኖር እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ።
ሌላው የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት የሚያረጋግጥ “የአስተዳደር ስርዓት አዋጅ” ረቂቁ እያለቀ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ ይህ አዋጅ የህዝብን መረጃ የማግኘት መብት የሚያረጋግጥ እንደሆነ ጠቁመዋል። መረጃ የማይሰጡ አካላትን ተጠያቂ የሚያደርግ፤ መረጃ ሲጠየቁ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ ምን እንደሰሩና ምን እንዳልሰሩ ለህዝብ በግልፅ ማሳየት ያለባቸው መሆኑን የሚደነግግ ሲሆን ከእንግዲህ ማንም አካል መረጃ የማይሰጥበት አግባብ እንደማይኖር ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2012
ግርማ መንግሥቴ