ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ አመራርነት ካመጧቸው እንስቶች መካከል የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ አንዷ ናቸው፡፡ ከእርሳቸው ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ ማናቸው ?
ወይዘሮ መአዛ፡- ስለ ግል ሕይወት ታሪኬ ብዙ የማይታወቅ ነገር የለም፡፡ ተወልጄ ያደኩት አሶሳ ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባም መጥቼ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ተምሬአለሁ፡፡ ከዚያም በኋላ የመንግሥት ሥራ ሠርቻለሁ፡፡ ዳኛም ሆኜ አገልግዬአለሁ፡፡ በሲቪል ማሕበረሰብ ውስጥ ሠርቼአለሁ፡፡ የሴት ሕግ ባለሙያዎች ማሕበርን ከጓደኞቼ ጋር በመሆን መስርተን ብዙ ተንቀሳቅሰናል፡፡ከዚያም በኋላ ለትምህርት ወደ ውጭ አገር ሄድኩ፡፡ ከመሄዴም በፊት በምርጫ 97 ከኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ጋር አንድ ዓመት ሠርቼአለሁ፡፡በተለይም በምርጫ 97 በጣም ጥሩ የሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይትም መርቼ ነበር፡፡ በኋላም አሜሪካን አገር ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኬኔቲከት ሄጄ በዓለም አቀፍ ግንኙነት በማስተርስ ዲግሪ ተመርቄአለሁ፡፡
ዋናው ሥራዬ በተባበሩት መንግሥታት በተለይም በኢሲኤ ውስጥ ነበር፡፡ እዛም ሆኜ የኮሚኒቲ ሥራ አልተውኩም፡፡ እናት ባንክን በማደራጀት ሴቶችን አሰባስቤ አመራር ሰጥቼአለሁ፡፡ እናት ባንክ የቦርድ ዳይሬክተር ሆኜ ልክ ሥራዬን ጨርሼ ወደ መደበኛ ሥራዬ ትኩረት እያደረኩ ሳለሁ ነው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን በፕሬዚዳንትነት እንዳገለግል ጥያቄ የቀረበልኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጥያቄው ሲቀርብልዎት ምን ተሰማዎት?
ወይዘሮ መአዛ፡- መጀመሪያ ያልጠበኩት ጥያቄ ነበር፡፡ እዛ እሠራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ አንድ ቀን ተመልሼ አገሬን እንደማገለግል አውቅ ነበር፡፡ ይሁንና የማላውቀው የነበረው በምን ሁኔታ? መቼ በምን ደረጃ? የሚለውን ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ጥያቄ ሲመጣ መጀመሪያ ያልተጠበቀ ነው፡፡ በኋላ ነገሩን እያሰብኩበት ከቤተሰብም ከጓደኛም ጋር እየተመካከርኩበት እየተቀበልኩት መጣሁ፡፡ ውሣኔው ቀላል አይደለም፡፡ ያሰብኩበት ነገር አልነበረም፡፡ በኋላ ላይ ግን ይሄ ልዩ አጋጣሚ ነው፡፡ አገራችን በልዩ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለችው፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ እንዲህ አይነት የታሪክ ዕድል ሲመጣ ወደኋላ ማለት አይገባም በሚል ወሰንኩኝ፡፡ ኃላፊነቱንም ወስጄ ቃለመሐላ ከፈፀምኩ በኋላ የሕዝቡን የአገር ውስጥ ሚዲያውን፤ የዓለም አቀፍ ሚዲያውን ስሜትና ድጋፍ ስመለከት ደግሞ ይሄን ሥራ በቃ መሥራት አለብኝ፡፡ ከመጀመሪያውም መጠራጠር አልነበረብኝም የሚል ስሜት አደረብኝ፡፡ ሥራ ከጀመርኩም በኋላ እንደውም ምነው ቀደም ብሎ እንዲህ አይነት ሥራ ብሠራ ኖሮ ስንት አስተዋጽኦ ማድረግ እችል ነበር በሚል በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቤተሰብ ልጆችዎትንስ በተመለከተ፣
ወይዘሮ መአዛ፡- ሁለት ሴት ልጆች አሉኝ፡፡ ሲያትል አሜሪካን አገር ነው ያሉት፡፡ አንደኛዋ አምና ነው የሄደችው፡፡ ሁለተኛዋ በዚህ ዓመት ሄዳለች፡፡ አንዷ በዚህ ዓመት ኮሌጅ ገባች፡፡ ሁለተኛዋ ደግሞ ገና ሁለተኛ ደረጃ ትምህት ቤት ናት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለቤተሰብዎ ስንተኛ ልጅ ነዎት ?
ወይዘሮ መአዛ፡- የኢትዮጵያ ቤተሰብ እንደምታውቀው ሰፊ ነው፡፡ እኔ አምስተኛ ልጅ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሁነው ከተሾሙ በኋላ በመጀመሪያው ቀን ውሎዎት ምን ሠሩ ?
ወይዘሮ መአዛ፡- ሰኞ ዕለት ነው ሥራ የጀመርነው፡፡ ከዛ በፊት ግን ሐሙስ ቃለ መሐላ ፈጽመን ዓርብ መጥቼ ነበር፡፡ ለአንድ ለሁለት ሰዓት ያህል ቆይቻለሁ፡፡ በመጀመሪያ ያደረኩት ነገር ግቢውን መጎብኘት ነበር፡፡ ስትወጡ ታዩታላችሁ በቀኝ በኩል አንድ በቅርስነት የተመዘገበ ሕንፃ አለ፡፡ ድሮ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ የነበረ ነው፡፡ እዛም ገብቼ አየሁኝ፡፡ ትንሽ ባለው አያያዝ በጣም አዘንኩኝ፡፡ ይሄን የመሰለ ታሪካዊ ቦታ በጥሩ ሁኔታ አልተያዘም፡፡ ብዙም ያሰበበት ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ከአስተዳደሩ ጋር አሁን ይሄ እንዲታደስ የፍትሕ ቦታም ስለሆነ ከዚህ ጋር የሚመጥን ድባብ እንዲኖረው ተነጋግረናል፡፡አስፈላጊው እድሳት እንዲደረግ በሂደት ላይ ነው፡፡ ሰኞ ከነባሮቹ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጋር ስብሰባ አድርገን የነበረውን ሁኔታ ያሉትን ሥራዎች ገለፃ ተሰጥቶናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በማረሚያ ቤት ያደረጉትን ጉብኝት እንዴት አዩት? ምን አስተዋሉ?
ወይዘሮ መአዛ፡- በመጀመሪያ ቃሊቲ ነው የሄድነው፡፡ ግማሽ ቀን እዛ ነው የቆየነው፡፡ ታራሚዎችን በየማደሪያ ቤታቸው ገብተን አየን፤ አነጋገርናቸው፡፡ ከዛ በኋላ ደግሞ አዳራሽ ስብሰባ ተጠርተው የስምንት ዞኖች ተወካዮች ያለውን ችግር ገልፀውልናል፡፡ በአንድ በኩል አያያዙን በተመለከተ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ከተለወጠ በኋላ በአመጋገባቸው፤ በጤና አጠባበቅ፤ በመኝታ ረገድ ብዙ ለውጥ አለ የሚል ነገር ተናግረዋል፡፡ ይሄ የሆነው የተወሰኑ ታራሚዎችም በመለቀቃቸው ነው፡፡ የቦታ ሽግሽግም ተፈጥሯል፡፡ አያያዛቸው ተሻሽሏል የሚል ነገር ነው የተናገሩት፡፡
ሌላው የሚናገሩት የፍትሕ ችግር ነው፡፡ ግማሹ ለረጅም ጊዜ ቀጠሮ ላይ ቆየሁ ነው የሚለው፡፡ ግማሾቹ ደግሞ በተለይ አሁን በምሕረት አዋጁ የተፈቱ ሰዎች አሉ፡፡ በተመሳሳይ የሙስና ጉዳይ ነው የታሰርነው ለምን አንፈታም የሚል ነው፡፡ አንዳንዶቹ ሰውስ ብንገድል ከባድ ጥፋትስ ቢሆን በአሸባሪነት የተከሰሱት ሁሉ ከተፈቱ እኛስ ለምን አንፈታም፣ የእኛ ጉዳይ ከአሸባሪነት ይብሳል ወይ የሚሉም አሉ፡፡ ቤተሰባችን ክልል ነው ያሉት፡፡ ስንቅ ለማቀበል እዛ ነው የሚመቸን የሚሉ አሉ፡፡ በጣም ብዙ በርካታ ብሶቶች ይነሳሉ፡፡ የውጭ አገር ሰዎች በዕፅ ዝውውር የታሰሩ አሉ፡፡
መጨረሻ ላይ ስንለያይ አቤቱታችሁን በጽሁፍ አምጡ ብለን አረጋጋናቸው፡፡ በጥሩ ሁኔታ ነው ውይይቱ የተጠቃለለው ብዬ አስባለሁ፡፡ መነጋገሩም ጥሩ ነው፡፡ ከሰዓት በኋላ ደግሞ በጊዜ ቀጠሮ ላይ ያሉ በተለይ በቡራዩና በአዲስ አበባ በተፈፀመው ጥፋት የተያዙ ወጣቶችን አግኝተናል፤ እነርሱም ብዙ ብሶት አቅርበዋል፡፡ አያያዛቸውን በተመለከተ ለውጥ መኖሩን ተናግረዋል፡፡ ስለ ቃል አቀባበል በፖሊስ በኩል ጫና እንደሌለው ተናግረው፤ ቶሎ ምርመራው ተጠናቆ ወይ እንከሰስ ወይ ነፃ እንውጣ የሚል ተገቢ የሆነ ጥያቄ ነው ያነሱት፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ፌዴራል ፍርድ ቤቶች በውስጥ ያሉበትን ዕይታ ለማመላከት ከ131 ዳኞች የተሰበሰበው ትንተና እንደሚያመላክተው 55 በመቶ የዳኝነት ነፃነትን የሚጎዳ ጣልቃ ገብነት መኖሩን፤ 63 በመቶ አድሎአዊ አሠራርና ሙስና በፍርድ ቤቶች ውስጥ እንደሚስተዋል፤ 86 በመቶ ለጉዳዮች እልባት ለመስጠት መዘግየት፤ 88 በመቶ ዳኞች አገልግሎት ለመስጠት የዳኝነት ጥራት ችግር ያለ መሆኑን፤ 82 በመቶ የሚሆኑት ችግሮች በማሕበረሰቡ ዘንድ አመኔታ የተቸረው ነው ብለው እንደማያምኑ የሚጠቁም መሆኑ ተመልክቶአል፡፡ እነዚህን ስር የሰደዱና የተጠራቀሙ ችግሮችን በማስወገድ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ተአማኒነትን ለመፍጠር ምን መደረግ አለበት ብለው ያምናሉ ?
ወይዘሮ መአዛ፡- ይህ እኛ ቢሮ ከገባን በኋላ የሰበሰብነው መረጃ ነው፡፡ ከመጣን ጀምሮ አንድ መጠየቅ ተዘጋጅቶ 360 ለሆኑ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ ለመጀመሪያ ደረጃና ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞችም ተበተነ፡፡ በዛም መሰረት አሰባስበን ያገኘነው ይህን አሃዛዊ ጠቋሚ መረጃ ነው፡፡ መረጃውን ያዘጋጁት ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ሰለሞን ናቸው፡፡ ሳይንሳዊ ባይሆንም ይሄ ከእናንተው ያገኘነው መረጃ ነው በማለት መልሰን ለእነርሱ ካቀረብን በኋላ በዛም አነሰ መግባባት አለ፡፡ ይሄንን የሚክድ የለም፡፡ ከችግሩ ጥልቀት አንፃር ትራንስፎርማቲቭ የሆኑ እርምጃዎች እንደሚያስፈልጉ ተመካክረን ነው የተለያየነው፡፡ ዳኞቹ በዋናነት የሚያነሱት እንደተባለው እኛ ሥራችንን እኮ በነፃነት ማካሄድ አንችልም የሚል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ማነው ጣልቃ የሚገባው?
ወይዘሮ መአዛ ፡-አስፈፃሚው ጣልቃ ይገባል፡፡ ከፖሊስ ጫና አለብን፡፡ ከዓቃቤ ሕግ ጫና ከተለያየ ቦታ ጫና ነበረብን ይላሉ፡፡ እኔ ደግሞ የምላቸው ምንድነው አሁን አዲስ አመራር ስለመጣ የዳኝት ነፃነትን ለማረጋገጥ ዳኞች ራሳቸው ለራሳቸው መቆም አለባቸው፡፡ ሲታዘዙ አቤት ከማለት ወጥተው የዳኝነት ነፃነትን ለማስከበር እያንዳንዱ ዳኛ መቆም መቻል አለበት ነው፡፡ ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡ ጥሩው ነገር ደግሞ አሁን የአስፈፃሚው አካላት ሪፎርሙን እየመሩት ያሉት ሰዎች የዳኝነትን ነፃነት ለማክበር ቁርጠኝት እንዳላቸው ነው በየቦታው እየገለፁ ያሉት፡፡ ይህ ትልቅ ዕድል ነው የሚመስለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የፍትሕ ዘርፉን ተአማኒነት የመመለስ ሥራ የቅንጅት ተግባር ነው፡፡ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ምን ይጠበቃል ?
ወይዘሮ መአዛ፡- የፍትሕ አካላት ኮሚቴ የሚባል አለ፡፡ ሰብሳቢው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ነው፡፡ እዛ ውስጥ የፌዴራል ፖሊስ፣ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስና የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች አሉበት፡፡ አቢይ ኮሚቴ ነው፡፡ በዛ ውስጥ እንግዲህ እንዳልከው የተቀናጀ ሥራ ካልተሠራ የሕዝብን አመኔታ ለመመለስና ለሕዝቡ ፍትሕን ለማድረስ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡
ፖሊስ በጊዜው መርምሮ ካላቀረበ፤ ዓቃቤ ሕግ በጊዜው አናግሮ ምስክሮቹን ማስረጃውን ካላቀረበ፤ ፍርድ ቤት ደግሞ በጊዜው ያንን መዝኖ ውሣኔ ካልሰጠ፣ እነዚህ አካላት ተቀናጅተው ካልሠሩና ሁሉም ሥራውን በተገቢው ቦታ፣ ጊዜና ጥራት ካልሠሩ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ የጋራ መድረኩ ስላለ በጋራ የሚሰሯቸው ሥራዎች አሉ፡፡ በቀጣይነት ደግሞ አሁን ካለው የአጣዳፊነት ስሜት አንፃር ምንድነው ማድረግ የምንችለው የሚለውን ደግሞ እየተነጋገርን ነው፡፡
በሌላ በኩል መታወቅ ያለበት ከነበሩት በተጨማሪ አዳዲስ ችግሮችም አሉ፡፡ አገሪቱ ውስጥ ያለመረጋጋት ሁኔታ አለ፡፡ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ ያንን የመከታተልና የመመርምር ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ችግሮች በሞብ (በመንጋ) ነው የሚፈጠሩት፡፡ ያን ደግሞ ተጨባጭ የሆነ ማስረጃ ቶሎ ላያገኙ ይችላሉ፡፡ ማስረጃ ባለማግኘት ደግሞ ጥፋት የሠሩ ሰዎች ሲለቀቁ ሕዝቡ በፖሊስ ላይ ምሬት ያቀርባል፡፡ በፍርድ ቤት በኩል ደግሞ ቶሎ ማስረጃ ካላቀረባችሁ እንለቃለን የሚል ነገር አለ፡፡ እውነቱን ለመናገር ጊዜው ከበድ ይላል፡፡ የወንጀል አይነቱም እየጨመረ እየበዛ እየተወሳሰበ መጥቷል፡፡ በዛ ላይ ደግሞ ፖሊስ የመርማሪዎቻችን የአቅም ውስንነት አለ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በአደጉት አገሮች በተለያየ ሳይንሳዊ ቴክኒክ ነው ምርመራ የሚደረገው፡፡ እዚህ የሚደረገው 90 በመቶ በማንዋል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኋላቀር የሆነውን አሠራር ለመለወጥ ምንድነው የሚደረገው ?
ወይዘሮ መአዛ፡- የአቅም ግንባታ፣ የሂደትና የጊዜ ነገር ነው፡፡ አመራር መስጠትና የውጭ ሀብት ማሰባብ (ሞቢላይዝ ማድረግ) ይጠይቃል፡፡ እኔ ሕዝባችንን መጠየቅ የምፈልገው ሰፊ ትእግስትና መረጋጋት እንዲኖረው ነው፡፡ የፍትሕ ጉዳይ በአንድ ጀምበር መልስ የሚገኝለትና የሚቋጭ አይደለም፡፡ እርጋታና ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ሪፎርሙ ተጀምሯል፡፡ መንግሥት መልካም ሐሳብ አለው፡፡ ሕዝቡ በቅን ልቦና እንዲረዳው ትእግስት እንዲያደርግ ያስፈልጋል፡፡ በአንዴ አይሆንም፡፡ የሚሆንም ነገር የለም፡፡ ሰክነን እያስተዋልን ከሄድን ብዙ የተበላሹ ነገሮችን በማስተካከል ታላላቅ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንችላለን፡፡
የሚዲያ ሰዎች እንዲከታተሉት እንዲያውቁት ሕዝቡንም እንድታሳውቁት የምፈልገው የሀሰተኛ ማስረጃ ሰነድ ጉዳይ ነው፡፡ በሀሰተኛ ሰነድ ሰው ንብረቱን እያጣ ነው፡፡ ይሄ ሀሰተኛ ሰነድ ደግሞ እንደሌላ ጊዜ ከመደበኛ መዋቅር ውጭ አይደለም የሚመጣው፡፡ ካርታ የሚሰጡትና ውል የሚፈጽሙት ሕጋዊ አካላት ናቸው፡፡ በዚህም በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ውጭ አገር ነበርኩ ቤቴ ተወሰደብኝ በሚል በብዛት አቤቱታ እያቀረቡ ነው፡፡ ፍርድ ቤት ደግሞ ማስረጃ ቀርቦልኛል ይላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ባለቤት ያልሆነ ሰው ሀሰተኛ ሰነድ አሰርቶ የሰው ቤት ይወርሳል፤ በፍርድ ቤት ያጸድቃል ይሄ እንዴት ነው የሚፈታው ?
ወይዘሮ መአዛ፡- አሁን አንዱ ሥራችን ከዛ ነው የሚጀምረው፡፡ ለምሣሌ የቤት ካርታ ባለቤትነት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማንም ገብቶ ሊደልዝና ሊሰርዝ በማይችልበት ሁኔታ በየመሥሪያ ቤቱ እንዴት ነው ሊረጋገጥ የሚችለው? የተቀናጀ አሠራር መኖር ከዚህ ነው የሚጀምረው፡፡ እንደነዚህ አይነት አሠራሮች ኮምፒተራይዝድ በሆነ ሲስተም የተረጋገጡ ቢሆኑ ዳኛ ትኩረት የሚያደርገው ሕጉን መተርጎም ላይ ይሆናል፡፡ ብዙ ጊዜ የሚጠፋው እውነቱን በመፈለግ ነው፡፡ ይሄም የእኔ ንብረት ነው ብሎ ያመጣል፤ ይሄም የእኔ ንብረት ነው ብሎ ያመጣል፡፡ ሕዝቡን ቢያንስ በአጭር ጊዜ ውስጥም ቢሆን ማሳወቅና ማንቃት ያስፈልጋል፡፡ እንደ ድሮው በሰነድ ብቻ ሳይሆን ይሄ ቤት የማነው ብሎ ቦታው ድረስ ሄዶ እስከ መጠየቅ ድረስ መድረስ አስፈላጊ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ካለው የገዘፈ ችግር አንፃር በየክፍለ ከተማው ኮሚቴዎች ቢቋቋሙና ተጠሪነታቸው ለእናንተ ቢሆን እክሉን ለመፍታት አይረዳም ? ሕዝቡን ብታገኙት ብታወያዩትስ የበለጠ የችግሩን ጥልቀት ለመረዳት አይቻልም ?
ወይዘሮ መአዛ፡- ይሄ ከፍርድ ቤት ሥራ ውጭ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች በቀረበው መረጃ መሰረት ፍርድ ሰጠን ነው የሚሉት፤ ትክክል ናቸው፡፡ ግን ደግሞ እንዴት ነው እንዲህ ብለን ዝም የምንለው ? ወይ ችግሩን ሚዲያ እንዲያውቀው ማድረግ ነው፡፡ ይሄ ችግር ያልተለመደ ስለሆነ ባልተለመደ መንገድ ለመፍታት መሞከር አለብን ነው የምለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ባሉት የፍትህ አሰጣጥ ችግሮች ዙሪያ ሕዝቡን ብታወያዩት ውጤት አያስገኝም?
ወይዘሮ መአዛ፡- እሱን ሥራ ጀምረናል፡፡ ባለፈው ሳምንት ከዳኞች ጋር ስብሰባ ነበረን፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት ከጠበቆች ጋር አለን፡፡ ከዚያ በኋላ ከፖሊስ ጋር ይቀጥላል፡፡ እንደገናም ከሕዝቡ ጋር ውይይት ይኖረናል፡፡ ተከታታይነት ያላቸው የግንኙነት መርሃ ግብሮች ነድፈናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በመላው አገራችን ማለት በሚቻል መልኩ የፍርድ ቤት መረጃዎች አያያዝን በተመለከተ መዝረክረኮች ይታያሉ፡፡ በተለይ ከአዲስ አበባ ውጭ ሲወጣ ፍርድ ቤቶች ንፁህና የተደራጀ ቢሮ የላቸውም፤ እርስዎ ምን ይላሉ ?
ወይዘሮ መአዛ፡- በፍርድ ቤቶችም በኩል እውነቱን ለመናገር በጣም ጥሩ የተሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡ እኔ እዚህ ተመድቤ ስመጣ ይሄን ያህል ትልቅ መሥሪያ ቤት አልመሰለኝም፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጣም ግዙፍ መሥሪያ ቤት ነው፡፡ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ብቻ 39 ዳኞች አሉ፡፡ የአሜሪካን ጠቅላይ ፍርድ ቤት 9 ዳኛ ብቻ ነው ያለው፡፡ ይሄ ጥንካሬም ድክመትም ሊሆን ይችላል፡፡ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች 500 አሉ፡፡ በጣም ግዙፍ ተቋም ነው፡፡ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከ100 በላይ ዳኞች አሉ፡፡ እንደገና ከ1000 በላይ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች አሉ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ብትሄድ እንደዛው፡፡ ይህ ደግሞ በተለያየ ጊዜያት አገራቸውን ባገለገሉ በነበሩ መሪዎች ኃላፊዎች ሠራተኞች ድካም ልፋት ጥረት የተገነባ ነው፡፡ ሊመሰገኑም ይገባል፡፡ በበርካታ ዓመታት በትውልድ ፈረቃ የተገነባ ቤት ነው፡፡
የአይቲን ጉዳይ በተመለከተ ጥሩ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ፡፡ የፋይሊንግ ሲስተም፤ ኦን ላይን ክስን የመክፈት ሁኔታ እንደገናም ደግሞ ከክልል ወደዚህ በይግባኝ የሚመጡ ሁኔታዎችን 42 የቪዲዮ ኮንፈረንስ የሚያካሄዱ ቦታዎች ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ ነገር ግን መስፋት አለበት፡፡ እሱን እየሠራን ነው፡፡ ሬጅስትራር አካባቢ ያሉ ችግሮች ከበፊቱ እጅግ በጣም በተሻለ ሁኔታ ነው ያሉት፡፡ ፍርድ ቤቶች ሌላ በጣም የሚቸገሩበት ጉዳይ ቦታ የሕንፃ ጉዳይ ነው፡፡ በየጊዜው ችሎቶች ይሰፋሉ፡፡ ምክንያቱም ሕዝቡም እየበዛ ነው፡፡ ክሱም ወንጀሉም የፍትሐብሔር ክሱም እየበዛ ነው፡፡ የዛኑ ያህል ፍርድ ቤቶች እስከ ዛሬም ድረስ ይሄንን ግዙፍ ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችላቸው ተመጣጣኝ የሆነ መዋቅራዊ ተቋም የላቸውም፡፡
አዲስ ዘመን፡-ለምን ?
ወይዘሮ መአዛ፡-ፍርድ ቤቶች እኮ ቀደም ብለን እንደተነጋገርነው ይሄን ያህል ከበድ ያለ ትኩረት የሰጣቸው የለም፡፡የፍትሕ ሥርዓቱን እኮ ከበድ አድርጎ የወሰደው የለም፡፡ አሁን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆኜ ስሾም ሰዎች ምንድነው ሥራው እሱ ይሉኛል፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ማለት ምን ያህል በሕገ መንግሥቱ ቦታ እንዳለው ሰው ገና አልተረዳም፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱና አስፈፃሚው
ወንድወሰን መኮንን