* ‘’መደመር’’ የተሰኘው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መፅሀፍ በአዲስ አበባ እና በ20 ከተሞች ተመርቋል
አዲስ አበባ፡- የመደመር ፍልስፍና ያለፈውን ወረት አጥብቆ መያዝ፣ የትናንቱን ስህተት ማረምና ነገን በአሸናፊነት ማለም እንደሆነ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ትናንት መፅሀፋቸውን በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ባስመረቁበት ወቅት ሲሆን የመደመር ፍልስፍና ሀገር በቀል የሆነና ከዚህ በፊት በየትኛውም ሀገር በማንኛውም ግለሰብ ይህንን ፍልስፍና አንድ ሀገር ካለችበት ችግር መሸጋገሪያ ይሆናል በሚል የቀረበ ሙሉ ሀሳብ አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡መፅሀፉ በትናትናው ዕለት በአዲስ አበባ እና በ20 ከተሞች ተመርቋል።
መደመር ልዩነት የለንም ብሎ አይነሳም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩነቶቻችን ጌጥ ሆነው ለአንድነታችን ምሰሶ መሆን ይችላሉ ብሎ እንደሚያምን ገልፀዋል፡፡ መደመር ያለፈውን ወረት አጥብቆ መያዝ ይህም ሲባል ወረታችን ለበርካታ ዓመታት ተከባብሮና ተቻችሎ የሚኖር የክርስቲያን እና ሙስሊም ሀገር ስላለን፣ መደመር የትናንቱን ስህተት ማረም ማለት ቢያንስ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአራት ሰዎች አንዱን የደሀ ደሀ የሆነበት በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ የዕለት ጉርስና መጠለያ የሌለው በእኛው ስህተት በመሆኑ እና መደመር ነገን በአሸናፊነት ማለም ደግሞ ድህነትና ችግርን የምናወርስ ሳይሆን ብልፅግናን ለልጆቻችን የምናሻግር እንድንሆን ያደርጋል ማለት ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፡፡
መደመር ሰው የመሆን እሴት ነው ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም መነሻውም መድረሻውም ሰውና ተፈጥሮ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በፊት አራት መፅሀፎችን መፃፋቸውን ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‘’ዲራአዝ’’ በሚል የብዕር ስም ሲጠቀሙ እንደነበር ጠቅሰው ‘’ሰተቴ’’ እና ‘’እርካብና መንበር’’ መጻፋቸውንና በተለይም ‘’ሰተቴ ስጋት’’ ውስጥ ሆነው በውስጣቸው የነበረውን ጩኸት ያሰሙበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በምረቃ ስነስርዓቱ የመፅሀፍ ዳሰሳ ያቀረቡት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሌንጮ ባቲ አሁን እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች ሀገር በቀል መፍትሄ የሚፈልጉ በመሆናቸው ደራሲው ከዚህ ተነስተው በሀገር በቀል ፍልስፍና የፃፉት መፅሀፍ ወደጋራ ብልፅግና የሚደረግ ጉዞን ያመላክታል ብለዋል፡፡
መፅሀፉ የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት ፣ የውጪ ግንኙነት፣ ኢኮኖሚያዊ እይታና ፓለቲካዊ እይታን አካቶ በአራት ዋና ዋና ክፍሎች የተፃፈ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ሌንጮ ደራሲው ፉክክርና ትብብር ሚዛናቸውን ጠብቀው አልሄዱም ብለው እንደሚያምኑም ገልፀዋል፡፡ መፅሀፉ ስህተትን አርሞና የተበላሸን አስተካክሎ ወደፊት መራመድን በግልፅ የሚያሳይ ሲሆን መደመር የዜጎችን ክብር የማረጋገጥ ቅድሚያ እንደሚሰጥ በዳሰሳው ተገልጿል፡፡
ዘላቂ የልማት አቅጣጫዎችን በማሳየት የማክሮ ኢኮኖሚው እንዲስተካከልና በአጭር ጊዜ ወደ እድገት ለማምራት ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚያሳይ የተነገረለት መደመር መፅሀፍ በውጪ ግንኙነት እይታው በጠላትነት የሚፈረጅ ሀገር አለመኖሩንና እድገት የሚሳለጠው ጎን ለጎን አብሮ መራመድ ሲቻል እንደሆነ፣ በሀገር ልማት የዳያስፖራው ተሳትፎ ጉልህ ነው ብሎ እንደሚያምንም አቶ ሌንጮ ተናግረዋል፡፡
ችግሮችን ትናንት እና ዛሬ ላይ ማላከክ፣ ሌብነት እና ታታሪ አለመሆን የመደመር እንቅፋቶች ሆነው ሊታዩ እንደሚችሉ የተናገሩት አቶ ሌንጮ የመደመር እሳቤ የሰው ልጅ ክብርና መብትን ያስቀድማል፤ የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ይፈታል፤ ህዝብን ሳይከፋፍል የጋራ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ይጥራል ሲሉ በዳሰሳቸው አመላክተዋል፡፡
ዶክተር ምህረት ደበበ በበኩላቸው መፅሀፉ ሀሳብና ሰው ሁሉን መስራት እንደሚችል ያሳያል ብለው መደመር ከሰው ማንነትና ዝምድና ጋር ያለውን ግንኙነት በዳሰሳቸው ለታዳሚያን አቅርበዋል፡፡ የፉክክርና ትብብር ጉዳይ መሠረታዊነትን ያስቀምጣል ያሉት ዶክተር ምህረት ሰው ወለድና ተቋም ወለድ ችግሮችን እንዲሁም የገዢነትና መሪነትን ልዩነትን ሁሉ በግልፅ ማስቀመጡንም አስረድተዋል፡፡
በእለቱ የኪነጥበብ ባለሙያዎቹ አዜብ ወርቁ፣ ሰርፀ ፍሬስብሀት፣ ፈለቀ የማርውሀ አበበ እና ተፈሪ አለሙ ከመፅሀፉ የተወሰኑ ገፆችን ለታዳሚያን ያነበቡ ሲሆን የክብር እንግዶቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ ቀዳማይ እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና ኢንጂነር ታከለ ኡማ መፅሀፉን ለተተኪ ተማሪዎች በስጦታነት አበርክተዋል፡፡
280 ገፆችን በያዘውና 300 ብር መሸጫ ዋጋ በተቆረጠለት በዚህ የመፅሀፍ ምረቃ ስነስርዐት ሚኒስትሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በተያያዘ ዜናም ‘’መደመር’’ የተሰኘውና በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የተጻፈው መጽሀፍ በባህር ዳር ፣ሃዋሳ፣ ሆሳዕና፣በጅግጅጋ፣ በሐረሪ ፣በድሬዳዋ ፣ በጎንደር እና በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች በጅማ፣በነቀምት፣በአዳማ ዐና በተሌ ቦታዎች የምረቃ ስነ ስርዓት ተካሄዷል።
በጎንደር ከተማ በተካሄደው የምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት፣ ነዋሪዎችና የሀይማኖት አባቶች የተገኙት ሲሆን በሚኒስትር ማዕረግ የኢህአዴግ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተፈራ ደርበው፥ መፅሐፉ ስለሀገራዊ ለውጡ በቂ ግልፅነትና መግባባት ይፈጥራል ብለዋል።
የለውጥ ሂደቱ ከውስጥም ከውጪም ከሚያስተናግዳቸው ትችቶች አንዱ ለውጡ የሚመራበት ግልፅ ፍኖተ ካርታ የለውም የሚል እንደሆነ አንስተው “መደመር” በሚል የተፃፈው መፅሀፍ ይህን ክፍተት እንደሚሞላ ተናግረዋል።
መፅሀፋ ለሀገራዊ ችግሮች ሀገራዊ መፍትሄን ለማሳየት እንዳለመ ገልፀው የ”መደመር” ሀሳብ ለመላው ኢትዮጵያውያን ተደራሽ እንዲሆን የታቀደ በመሆኑ መፅሀፋን በማንበብ ማዳበር የሚያስችል ግብአትና ለማረም የሚያስችል ትችት፤ አንብቦ በመረዳት ለሀሳቡ ተግባራዊነት ተነሳሽነትና ተጨባጭ አስተዋፅኦ ማበርከት ከኢትዮጵያውያን የሚጠበቅ ነው።
እንዲሁም በአዳማ ከተማ በተካሄደው “መደመር” መፅሃፍ ምረቃ ላይም የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ማእከላዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋን ጨምሮ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የከተማዋ ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን
የኦዲፒ ማእከላዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ባስተላለፉት መልእክት ሀገሪቱ ከዚህ ቀደም ፊውዳሊዝም፣ ሶሻሊዝም፣ ካፒታሊዝም እና አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፍልስፍናን ተጠቅማለች፤ ሆኖም ግን እነዚህ ፍልስፍናዎች በእኛ ልክ ያልተዘጋጁ በመሆናቸው፤ የህዝቡን ጥያቄ መመለስን ቀርቶ ለረሃብ እና ለችግር ሲዳርገን ነበር ብለዋል።
ከሁሉም በላይ የሀገር ውስጥ ባህል፣ እሴት እና እውቀትን መጠቀም አለመቻል ደግሞ ትልቁ ጉድለት ተደርጎ እንደሚወሰድ ነው የጠቀሱት።
ያሳለፍነው አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ በርካታ አዳዲስ ነገሮችን እና ተስፋዎችን ይዞ የመጣ ነው፤ በዚህ አጭር ጊዜ በርካታ ተግባራት ተሰርተዋል፤ ይህም ህዝቡ ዘንድ መነቃቃትን ፈጥሯል።
አሁን የተጀመረው ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው አዲስ የፍልስፍና ሀሳብ ማቅረብ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፤ በዚሁ መሰረት የሀገር ውስጥ እውቀት፣ እሴት እና ባህልን መሰረት በማድረግ እንዲዘጋጅ ተደርጓል።
የመደመር ፍልስፍና የጠቅላይ ሚኒስትር ሀሳብ ቢሆንም ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ሰላም እና እድገት ጉልህ ሚና ያለው ነው ያሉ ሲሆን፥ በህዝቡ እንዲዳብርም ቀርቧል ብለዋል።
ድህነትን ለመቀነስ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ጥረት የሚሻ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን በማድረግ ለሀገሪቱ እድገት መረባረብ አለበት።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2012
በድልነሳ ምንውየለት