አዲስ አበባ፡- የኢህአዴግ ውህደት መጨፍለቅ እንደሆነ እና ወደ አሀዳዊ ስርዐት መመለስ አድርጎ ህዝብን ማደናገር ተገቢ አለመሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ አስገነዘቡ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፓርቲ ውህደት ጋር ተያይዞ ለመላ ኢትዮጵያውያን ባስተላለፉት መልእክት የፓርቲ ውህደት ጉዳይ አለማለቁን ገልፀው ውይይቱ ሳይቋጭ አንዳንዶች ይህ ውህደት መጨፍለቅ እንደሆነ እና ወደ አሀዳዊ ስርዐት መመለስ አድርገው ህዝብ እያደናገሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ዓብይ በንግግራቸው የፓርቲ አንድ መሆን ኢትዮጵያን የሚጨፈልቅ ከሆነ ኢትዮጵያ አልነበረችም ማለት ነው ፤ የኢህአዴግ ውህደት መጨፍለቅ ነው የሚሉ አሉ፤ ይሄ ስህተት ነው፤ እውነት ነው ካልን በትግራይም በአማራም በደቡብም ያሉ ገዥ ፓርቲዎች ሌሎችን ብሄሮች ጨፍልቀው ነበር የኖሩት ማለት ነው ብለዋል፡፡
አንድ ፓርቲ መሆንና “መደመር” የማያዋጣ ከሆነ ጀግና የሆነ ሰው ውስኪውን አስቀምጦ “መባዛት” የሚል አማራጭ ይዞ ይቅረብ ያሉት ዶክተር ዐቢይ አህመድ መደመር ውስኪ ጠጪ ኢህአዴጎች እባካችሁ ውሃ መጠጣት የናፈቀው ህዝብ አለና አትርሱ ይላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እኔ ያልኩት ካልሆነ አገር ይፈርሳል ማለት የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያረጀ አስተሳሰብ ነው፤ በድጋሚ ላረጋግጥላችሁ የምወደው ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች፤ ካለችበት ከፍ ትላለች፤ ኢትዮጵያ እንዳትበለጽግ የሚፈልጉ ይጠፋሉ እንጂ ኢትዮጵያ አትጠፋም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ከዓመት እስከ ዓመት በ5 ሺህ ብር ደመወዝ ሆቴል እየተመገቡ ዳቦ የራበውን ህዝብ አስብልሃለሁ ማለት ዘበት እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዴሞክራት መሪ ስለሆንኩ ኢህአዴግ እንዴት እንደሚዋሀድ ምን ስም ይዞ እንደሚመጣ ሃሳብ አቀርባለሁ እንጂ እኔ አልወስንም፤ የተወሰነውን በቅርቡ ለህዝቡ እንገልጻለን ብለዋል፡፡
የሚቀጥለው ምርጫ የምናላግጥበት ሳይሆን የተሻለ ሀሳብ ይዘን የምንወዳደርበት ይሆናል ያሉት ዶክተር ዐቢይ ኢትዮጵያዊያን መገዳደልን አስወግደን በሀሳብ መታገልን ልንለምድ ይገባልም ብለዋል፡፡
ሰላም ሰላም የምንለው ጦርነትን ስለምንፈራ ሳይሆን ሰላምን አብዝተን ስለምንወድ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ ከኤርትራ ወንድም ህዝብ ጋር የተጀመረው ጉዞ ወደ ብልጽግና እንደሚደርስም ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2012
በድልነሳ ምንውየለት