አዲስ አበባ፡- የሕወሀት/ትህነግ/ አመራር የትግራይ ሕዝብን የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የፍትሕ እና የዴሞክራሲ እጦት ችግሮች ሳይፈታ ራሱን ከህዝቡ ጋር አንድ አድርጎ ማቅረቡ ተገቢ እንዳልሆነ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥና በትግራይ ሕዝብ ላይ ያለውን የወደፊት አንድምታ እንዲሁም በለውጡ ዙሪያ የራሱን ሚና አስመልክቶ በትናንት ዕለት በአዲስ አበባ ውይይት አካሄደ፡፡
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት)ትላንት በአዲስ አበባ ሀገር ፍቅር ቲያትር አዳራሽ ከአባላቱ ጋር ባካሄደው ውይይት ላይ የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሀ በኢትዮጵያ ያለው መከፋፈል እና መካረር ቀርቶ አንድነት እንዲጠነክር በየቦታው የሚነሱ ጥያቄዎችን በትብብር መፍታት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
‹‹ካልተሰባሰበ ትልቅ ሀገር ይልቅ የተሰባሰበች ትንሽ ሀገር ቁም ነገር ትሠራለች›› ያሉት ዶክተር አረጋዊ ‹‹የትህነግ አመራር የትግራይ ሕዝብን የመልካም አስተዳደር ችግር እና ፍትሕና ዴሞክራሲ ሳያስከብር ፓርቲውንና ሕዝቡን ‹አንድ ነው› ብሎ መናገሩ ተገቢ እንዳልሆነም ጠቁመዋል፡፡
ዶክተር አረጋዊ እንዳሉት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሆኑትም ጥቂት ግለሰቦች ናቸው፤ ይህ ሕዝቡ ላይ የሚፈጥረውን ውዝግብ ማቆም አለበት፤ ይህንንም ለመታገል የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲሰፋ ይሠራል ፡፡
የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉ ብርሃን ኃይለ በትግራይ አማራጭ ሐሳቦች በማስተናገዱ እንዲሁም ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማክበሩ ረገድ ውስንነት አለ ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በክልሎች መካከል እያታዩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር የበኩሉን ሚና ለመጫወት ጥረት እያደረገ መሆኑ ጠቅሰዋል። «ቀጣይ ትውልድ» በሚል መሪ ሐሳብ የአማራና ትግራይ ክልል ወጣቶች የሚሳተፉበት የጋራ መድረክ ለማሰናዳት እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም ቃል አቀባዩ አቶ ሙሉብርሐን ሃይለ ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የፓርቲው አባላት፣ ደጋፊዎች፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) ዓላማና ፕሮግራሙን አስመልክቶ ግንዛቤ የማስጨበጫ የተለያዩ ጽሑፎች እና አላማዎቹን የሚያስተገብርበት መስመሮቹን አቅርቧል፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2012
አብርሃም ተወልደ