አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የሚገኙ ጥብቅ ቦታዎች በቂ ትኩረት ባለማግኘታቸው እየተጎዱ መሆናቸውን የእጽዋት ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው ገለጹ፡፡
ፕሮፌሰሩ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ መንግሥትና ህብረተሰቡ ለእጽዋት ሀብት እንዲሁም ለጥብቅ ቦታዎች ትኩረት እየሰጠ ባለመምጣቱ ጥብቅ ቦታዎቹ እየተጎዱ እንዲሄዱ አድርጓቸዋል፡፡ የጥብቅ ቦታዎቻችን ከጠፉ በአገር ደረጃ የእጽዋት ሽፋናችን ያሽቆለቁላል፡፡
ይህ ደግሞ በህይወት የመኖርን ህልውና ይፈታተናል፡፡ ስለዚህም ምሁራን ህዝቡም ሆነ የሚሰራው አካል ሳይንሱን የሚረዱበትን መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ በተለይ አንዳንድ ክልሎች ላይ ያለው ሀብት ብዙ ቢሆንም መጠቀሙና እንክብካቤ ማድረጉ ግን ትኩረት ስላልተሰጠው ማሰብ ይገባል፡፡
የጥብቅ ቦታዎች መጎዳት መሰረቱ መንግሥት ብቻ ሳይሆን በአካባቢው የሚኖር ማህበረሰብ ጭምር እንደሆነ የሚናገሩት ተመራማሪው፤ በአገሪቱ ካሉት የተፈጥሮ ደን ቃጠሎዎች ውስጥ በስፋት የሚከወነው በሰዎች ነው፡፡ ይህ የደን ቃጠሎ ወይም ምንጠራ መገታት ካልቻለ ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በላይ አገር አደጋ ያጋጥማታል ብለዋል፡፡
የጥብቅ ቦታዎች ጉዳት ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ እንደመጣ የሚናገሩት ፕሮፌሰር ሰብስቤ ፤ የጥብቅ ቦታዎች ትኩረት እንዲያገኝ ከአንዳንድ ጓደኞቻቸው ጋር የሀሳብ ማመንጨት ሥራ ጀምረዋል፡፡ በአፍሪካም ደረጃ የእጽዋት ሳይንስን በሚመለከት ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው፡፡
ስለዚህ ብዙ ልምድ የሚገኝባቸውን መንገዶች ተጠቅሞ ማህበረሰቡንም ሆነ ሰራተኛውን ማሰልጠንና ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህ ምቹ የሚሆኑት በየአካባቢው ያሉት ዩኒቨርሲቲዎች እንደሆኑ ገልጸው፤በቅርቡ በሱማሌ ላይ ብዙ የእጣንና ከርቤ ምርት ማግኘት እንደሚቻል ስለሚታወቅ ስራዎችን ለመስራት ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ጋር መመካከራቸውን አንስተዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ገለጻ፤ መንግሥት ለጥብቅ ቦታዎች የሚሰጠውን ትኩረት ነገ የሚል ከሆነ የሚመጣው አደጋ ቀላል አይደለም፡፡ በተለይ ለረጅም ችግር መፍቻነት ያገለግላሉ ተብለው እየተሰሩ ያሉት ግድቦች ዋጋ ያጣል፡፡ በውሃ ሳይሆን በደለል ተሞልተው ጥቅም ሳይሰጡ ይቀራሉ፡ ፡
ስለሆነም የጥብቅ ቦታዎች ዋጋ ከፍ ያለ ትኩረት ሊቸረው ይገባል፡፡ የቦታዎቹ ጉዳት እንዳይልቅ ከምሁራን የሚሰጠውን ምክረሀሳብና የምርምር ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው