አዲስ አበባ፤ ያለፉት ምርጫዎች ብዙ ችግሮች የታዩበትና የመታዘብ መብት የተነፈገበት ስለነበር ስህተቱ በዘንድሮው የምርጫ ሂደት እንዳይደገም እየሰሩ መሆኑን የሲቪክ ማህበራት አስታወቁ፡፡
የክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ድርጅት ማህበራት ህብረት ዋና ዳይሬክተርና የሲቪክ ሶሳይቲ ፎረም የቦርድ ሊቀመንበር ዶክተር ንጉሱ ለገሰ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ያለፈው ምርጫ እንዳንታዘብ የታገድንበትና መብታችንን የተነጠቅንበት ነበር፡፡
ይህ ችግር ዳግም እንዳይከሰትና ለህዝብ ታማኝ ለመሆን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ለአገራዊ ምርጫም ሰባት ማህበራት የተሳተፉበት አብይ ኮሚቴ አቋቁመን በሥራ ላይ ነን፡፡
የሲቪክ ማህበራት አዋጁ መሻሻሉ ትልቅ ሞራል እንደፈጠረላቸው የሚናገሩት ዶክተር ንጉሱ፤ ከዚህ ቀደም በነበረው ምርጫ ሲቪል ማህበራት በምርጫ ትምህርት መስጠት ዙሪያ እንዲሳተፉ አይፈቀድም፡፡ ዋና ሥራቸው መታዘብ ብቻ ነበር፡፡ ስለዚህ ዴሞክሪሲያዊ፤ ነጻና ተአማኒ ምርጫ መካሄዱን ታዝበናል ማለት አይቻልም፡፡
አሁን መንግሥት ሰፊ እድል ያጎናጸፈን በመሆኑ በተለያየ መንገድ የማስተማሩን ሥራ ለማከናወን የአሰልጣኞች ስልጠና እየሰጠን እንገኛለን፡፡
የሲቪክ ማህበረሰብንም በምርጫ ዙሪያ ለማስተማር የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸው እስካሁንም 403 የሚደርሱ አባላት በምርጫው ዙሪያ ለመሥራት እንደተመዘገቡ ተናግረዋል፡፡ ሲቪክ ማህበራት በመንግሥትና በህዝብ መካከል ትልቅ ድልድይ በመሆን እንደሚያገለግል ጠቅሰው ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን በተቻለ መጠን እንሰራለን ብለዋል፡፡
በተለይ በምርጫ ትምህርት ስልጠናና በመታዘቡ ዙሪያ ለመስራት አስቻይ ሁኔታ ከሌሎች የውጪ ዜጎች ጋር በመሆን ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
በምርጫው ዙሪያ ምን ተግባራትን እንደምናከናውንም ስትራቴጂክ እቅድ አውጥተን የተግባር ሥራ ላይ ገብተናል። ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ ሆኖ ለመስራት ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረንስ ፎር ዴሞክራሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደለ ደርሰ በበኩላቸው፤ አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫውን በጣም አሳሳቢ የሚያደርገው የሰላም ጉዳይ መሆኑን ያነሳሉ፡፡ሆኖም በምርጫው ዙሪያ ለመስራት የሚያስችላቸውን መመሪያ ከምርጫ ቦርድ እስኪመጣ እየጠበቁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እስካሁን ነጻ፣ዴሞክራሲያዊ እና ተአማኒነት ያለው ምርጫ እንዲከናወን ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች አለመሰራታቸውን ጠቅሰው፤ በዘንድሮ ምርጫ ክፍተቶችን ለይተው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሲቪክ ማህበራቱ ከእስካሁኑ ስህተት ተምረውና በደረሰበት በደል ሳይከፉ ለአገር መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ ሰላማዊ ምርጫ በአገሪቱ እንዲከናወንም ማገዝ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ምርጫው በተቻለ መጠን ባለፉት ምርጫዎች ያጋጠሙን ግድፈቶች በሚያርም መልኩ መሆን ይኖርበታልም፡፡ ነጻና ዴሞክራሲያው፣ ተአማኒነት የሞላበት፣ በፖለቲካ ልሂቃንና የምልአተ ህዝቡን ተሳትፎ ያረጋገጠ እንዲሆን የመንግሥት ቁርጠኝነትና ዝግጅት ብቻውን በቂ አይደለምና የሲቪክ ማህበራት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው