አዲስ አበባ፡- ከመንግሥት ፖሊሲ ጋር ተናበው ባለመስራታቸው ሰማንያ ነጥብ ሰባት በመቶ የግል ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ሥልጠና፤ ጥራት ሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
ባለስልጣኑ ትናንት በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ እንደገለፁት፤ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ብዙ ሥራ ቢሠራም አሁንም በግልና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ የሆነ ችግር ይስተዋላል፡፡ ከ2009 ዓ.ም እስከ 2011 ዓ.ም በተደረገው የኢንስፔክሽን ሥራ በርካታ የግልና የመንግሥት ተቋሞች ከመንግሥት በወረደ አቅጣጫ ባለመስራታቸው ከደረጃ በታች ናቸው፡፡
በባለስልጣን የኢንስፔክሽን ቡድን መሪ አቶ መልካሙ ፀጋዬ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ እንደጠቆሙት፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በርካታ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ናቸው፤ ማለትም ደረጃ አንድና ሁለት ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ የግል ትምህርት ቤቶች የሀገር ውስጥ የትምህርት ካሪኩለምን አለመከተል፣ ምቹ የሆነ የመማር ማስተማር ሒደት አለመኖርና የተለያዩ ሀገራት የትምህርት ፖሊሲዎችን ከውጪ በመቅዳት በትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ አስተዋፅኦ እያስከተሉ ነው፡፡
እንዲሁም ከሚመለከተው አካል እውቅና ውጭ በራሳቸው መፅሀፍ ማሳተምና ማስተማር ፣ የሀገራችንን የትምህርት ፖሊሲ የማይቀበላቸውን የመማር ማስተማር ስርዓትን መዘርጋትና ከሙያ ውጭ የሆኑ መምህራንን ቀጥሮ እንዲያስተምሩ በማድረግ ተማሪዎች በደረጃቸው ማግኘት ያለባቸውን እውቀት እንዳያገኙ ሆነዋል፡፡
አቶ መልካሙ አክለውም ይህ ሁኔታም በርካታ የግል ትምህርት ቤቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ከደረጃ በታች እየሆኑ እንዲመጡ አድርጓቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከመንግስት ትምህርት ቤቶች ጋር ሲነፃፀር 73 ነጥብ7 የመንግሥት፣ 80ነጥብ 7 የግል በድምሩ 79 ነጥብ 3 ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ናቸው፡፡
በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ደግሞ መምህራን የሚጠበቅባቸውን ያህል ጊዜ አለማስተማርና ከስራ መቅረት የትምህርት ጥራት በፍጥነት እያሽቆለቆለ እንዲመጣ አድርጎታል፡፡ በዚህም ምክንያት በ2011 ዓ.ም በከተማ መስተዳድሩ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች አነስተኛ ውጤት እንዳስመዘገቡ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2012
ሞገስ ፀጋዬ