አዲስ አበባ:- በ2011 በጀት ዓመት ከተገነቡ 157 የፋብሪካ ሼዶች መካከል 129ኙ ለባለሀብቶች በኪራይ መልክ መተላለፋቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አማረ አስገዶም እንዳሉት በበጀት ዓመቱ ከተከራዩት የፋብሪካ ሼዶችና ከሌሎች ህንፃዎች ኪራይ፣ ከለማ መሬት ሊዝና ከልዩ ልዩ ገቢዎች በድምሩ 457 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ለማግኘት ታቅዶ 316 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ገቢ ተገኝቷል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አማረ አስገዶም ለዝግጅታችን ክፍል አስታውቋል።
አፈፃፀሙ ከዕቅዱ ያነሰበትም ምክንያት በዕቅዱ መሰረት ሙሉ በሙሉ የፋብሪካ ሼዶች በባለሀብቶች ባለመያዛቸውና ውል የተዋዋሉ ባለሀብቶችም ዘግይተው ሼዶቹን በመረከባቸው መሆኑ አቶ አማረ ተናግረዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ በ2012 በጀት ዓመት ልዩ ትኩረት በመስጠት ገቢውን አሟጦ የመሰብሰብ ሥርዓት እንዲዘረጋ በማድረግ ኮርፖሬሽኑ ወደ ትርፋማነት የሚያሸጋግር ሥራ ይሠራል ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአብዛኛው የሚጠበቁት የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እንዲረዱ ነው ያሉት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ፣ መንግሥት የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የፋብሪካ ሼዶችን በመገንባት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ማዕከል አድርጎ እያከራየ መሆኑም ተናገረዋል።
ከውጭ የሚመጡ ባለሀብቶች በቀጥታ ወደ ምርት ሥራ እንዲገቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመወዳደር የሚያስችላቸው የተሟላ መሠረተ ልማት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ሼዶቹ በ6ት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ኦፕሬሽን በማስገባት ኤክስፖርት መጀመር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በዘርፉ እውቀት ያላቸው ባለ ሀብቶች መጥተው ሥራቸውን እንዲሠሩ መንግሥት ለባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑ ተናግረዋል።
የውጭ ባለ ሀብቶች በቴክኖሎጂና በካፒታል የተሻሉ በመሆናቸው በአብዛኛው ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገቡት አጋጠሚ እንደሚበዛ የጠቆሙት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ፤ የውስጥ ባለ ሀብቶች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከውጭ ባለሀብቶች ማስተሳሰር ፣ በቴክኖሎጂና በፋይናንስ አቅም የማሳደግ ና የመደገፍ እንቅስቃሴ እንደ አንድ ስትራተጂ ተይዞ በስፋት እየተሠራበት መሆኑንም አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2012
በማዕረግ ገ/እግዚአብሔር