አዲስ አበባ፡- የአዕምሮ ጤና ህክምና አገልግሎት በቂ ባለመሆኑ በአገሪቷ ከመጀመሪያ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ባሉት ሆስፒታሎች 25 በመቶ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የዘርፉ ኤክስፐርት ገለጹ።
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የአዕምሮ ጤና ኦፊሰር የሆኑት ሳይካትሪስት ዶክተር ደረጄ አሰፋ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በአዕምሮ ጤና ችግር ላይ የተሰሩ ጥናቶችን መነሻ በማድረግ ችግሩን በሂደት ለማቃለል ከሚሰሩ ሥራዎች መካከል አገልግሎቱን በአገር አቀፍ ደረጃ ባሉት ሆስፒታል 25 በመቶ ተደራሽ ማድረግ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአዕምሮ ጤና እክል ያለባቸው ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ተከትሎ በኢትዮጵያም አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ችግሩ እየተስፋፋ እንደሆነና በሆስፒታሎች ደረጃ አገልግሎቱን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ዶክተር ደረጄ አስታውቀዋል።
በመሆኑም፤ የአዕምሮ ጤና ህክምና አገልግሎት በቂ ባለመሆኑ በአገሪቷ ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ባሉ ሆስፒታሎች ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ያሉትንና የማይሰጡትን የጤና ተቋማት በመለየት፤ አገልግሎት የማይሰጡ ሆስፒታሎች ወደ አገልግሎት እንዲገቡ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዘርፉን ለማጠናከር መሪ እቅድ መዘጋጀቱን የገለጹት ዶክተር ደረጄ፤ እቅዱ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲዘጋጅ መቆየቱንና አሁን ላይ መሳካቱን ገልጸዋል። በጤና ሴክተሩ ማህበረሰቡ በአዕምሮ ጤና ላይ ያለውን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራም እየተሰራ ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት 80 ከሚደርሱ የጤና ማዕከላት ለተመረጡ የጤና ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት የአዕምሮ ጤና አገልግሎት በሰፊው እንዲጀመር መደረጉን ገልጸዋል።
አገልግሎቱን በማስፋት ደረጃ በጤና ሚኒስቴር በኩል የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ተቋማትን በዘርፉ ደረጃቸውን የጠበቁና የተሻለ ጥራት ያላቸው ለማድረግ የአዕምሮ ጤናን ያካተተ “ጋይድ ላይን” ተዘጋጅቶላቸው እየሰሩበት ይገኛሉ። በዚህም መሠረት ማንኛውም ባለሙያ የአዕምሮ ጤና ችግር ያለባቸውን የመለየትና የማከም ሥራ በቀላሉ ለማከናወን ያስችለዋል። ይህም ከ500 በላይ ጤና ጣቢያዎችን ተደራሽ ማድረግ ችሏል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2012
አዲሱ ገረመው