የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ በወቅታዊ ሀገራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ የፖለቲካ ምሁራን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣ የቀድሞ የህወሓት አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች የተገኙበት ውይይት አካሂዶ ነበር፡፡ በመድረኩ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ በረከት ስምዖን ሲሆኑ፤ ሰፊ ውይይቶችም ተካሂደዋል፡፡ በውይይቱ ወቅት የዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉዓላዊነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ አስተያየት በመስጠት ላይ እያሉ በጭብጨባ እንዲያቋርጡ መደረጉ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ጉዳይ ሆኖ ከርመሟል፡፡ አዲስ ዘመን ከአቶ ዓምዶም ጋር ቆይታ አድርጓል፤ ያንብቡት፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው ስብሰባ ሃሳብዎትን ሳይጨርሱ በጭብጨባ እንዲያቋርጡ ተደርጓል፤ በስብሰባው ያነሷቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ምንድን ነበሩ?
አቶ ዓምዶም፡- ውይይቱ ወቅታዊ የሀገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ ምን ይመስላል፤ ተግዳሮቶችና መልካም ዕድሎቹስ ምንድን ናቸው? የሚል ነው፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ሁኔታም በርዕሰ ጉዳይነት ተነስቷል፡፡ የእኛም ፓርቲ ተጋብዞ ነበር፡፡ አቶ በረከት ስምዖን ኢህአዴግ የሕግ የበላይነትን እያስከበረ አይደለም፤ የሀገሪቱ አካሄድም አደገኛ ነው የሚል አስተያየት አቅርበዋል፡፡
እኔ ደግሞ ኢሕአዴግ የለም፣ ሊጠፋ ተቃርቧል የሚል አስተያየት ሰጥቻለሁ፡፡ አሁን የፖለቲካ ምሕዳሩን ለማስፋት የተደረገው ጥረት፤ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመላው ዓለም ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ የተወሰደው እርምጃ፤ የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ጥረት፤ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ሌሎችንም ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ለማድረግ እየተካሄደ ያለው ጥረት መልካም እንደሆነ ገልጫለሁ፡፡ ህወሓትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ናቸው የሚል የተለመደና የተሳሳተ ፕሮፓጋንዳ አለ፡፡ ይሄ ትክክል እንዳልሆነና ያለው በጣም አምባገነን መንግሥት በመሆኑ ከጭቁኑ ሕዝብ ጋር እንደ አንድ መታየት እንደሌለበት ማብራሪያ ለመስጠት ሞክሬ ነበር፡፡ በመካከል በጭብጨባ አቋርጠውኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጭብጨባ ባያቋርጡዋት ለመግለጽ ያሰቡት ቀሪ ሀሳብ ምን ነበር ?
አቶ ዓምዶም፡- ኤፈርትን በኃላፊነት ያገለገሉት አቶ ስብሀት ነጋ መድረኩ ላይ ስለነበሩ ባያቋርጡኝ ድርጅቱን በተመለከተ ለመናገር ነበር ያሰብኩት፡፡ ከኤፈርት ጋር በተያያዘ የትግራይ ሕዝብ ተጠቃሚ እንደሆነ ተደርጎ ይወራል፡፡ ህወሓት ድርጅቱን ለራሱ ነው መጠቀሚያ ያደረገው፡፡ ይሄ ድርጅት ለትግራይ ሕዝብ ጠቅሞ እንደማያውቅ፤ በትግራይ ላይ ያለው አፈና፤ የዴሞክራሲና የፍትህ እጦት፤ የፖለቲካ ምሕዳሩ ጠባብ መሆን፤ በሀገሪቱ ያለው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታም ጥንቃቄ ሊደረግበት እንደሚገባ ለመግለጽ አስቤ ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡- በመድረኩ ላይ በሰነዘሯቸው ሀሳቦች ከህብረተሰቡ ምን አይነት ምላሽ አስተናገዱ ?
አቶ ዓምዶም፡- መድረኩ ሀሳብን የመግለጽና የመናገር ሕገ መንግሥታዊ መብት በትግራይ በጣም የማይቻል መሆኑን፤ ከትላልቅ መሪዎች እስከ ተራው ካድሬ ሕዝቡን አፍነውት እንደነበረ ያሳየ ነው፡፡ እኔ የነበረውን አማራጭ ተጠቅሜ ሀሳብ በመሰንዘሬ አብዛኛው ሰው ድጋፍ አድርጎልኛል፡፡ አዳራሽ የነበሩት ቢቃወሙኝም ብዙዎችም በአካልም በማሕበራዊ ሚዲያም የደረሰብኝን አፈና እያወገዙና የተናገርኩት ሀሳብም ጥሩ እንደነበረ ነው እየገለጹልኝ ነው ያለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከመድረኩ የተሰነዘረው ተቃውሞ እንዲሁም ከሌላው ህብረተሰብ የተሰጠዎት ድጋፍ ከምን የመነጨ ይመስልዎታል?
አቶ ዓምዶም፡- ህወሓት ከፍተኛ ኔትወርክ አለው፡፡ እዚያ የሚገኘው ሚዲያ ከእነርሱ አመለካከት ውጭ ሌላ ነገር አያስተናግድም፡፡ እነዚህና ሌሎችም ተጨምረው ነው አፈና የሚደረገው፡፡ መሪዎቹ እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲመጣ ስለሚደናገጡና ሁሉ ነገር በሥራችን ነው ያለው የሚል እምነት ስለሚያሳድሩ ነው ተቃውሞ የተሰነዘረው፡፡ የእኛ ድምጽ ደግሞ ሁሌ እንደታፈነ ነው፡፡ ድምጻችንን የምናሰማበት አማራጭ ሚዲያ የለም፡፡ ህብረተሰቡ ደግሞ በተለይ ከትግራይ ውጪ ያለው ሰው የትግራይ ሕዝብና ህወሓት አንድ ናቸው የሚለውን የድርጅቱን ፕሮፓጋንዳ ይቀበላል፡፡ እንዲህ አይነት የተለየ ሃሳብ መኖሩን ሲሰማ ድጋፍ ይሰጣል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ እንደ መፍትሄ የሚሰጡት አስተያየት ምንድን ነው ?
አቶ ዓምዶም፡- ሁሉም ፓርቲዎች ሀሳባቸውን የሚያቀርቡበት ዕድል ቢያገኙ ጥሩ ነው፡፡ በፌዴራል በኩል ያሉትና ሌሎች ሚዲያዎችም አማራጮችን መዝጋት የለባቸውም፤ የእኛን ሀሳብ ሊያስተላልፉ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የትግራይ ሕዝብ በርካታ ጥያቄዎች አሉት፡፡ ታፍኖ ነው እየቀረ ያለው፡፡ የፌዴራል ሚዲያዎች ወደ ትግራይ ተንቀሳቅሰው ለሕዝቡ ሀሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ቢሰጡና ሀሳቡን ቢያዳምጡ ከፍተኛ ውጤት ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢ ዎች ግጭቶች ይታያሉ፤ መሰረታዊ ምክንያቶች ምንድን ናቸው ተብሎ ይታሰባል?
አቶ ዓምዶም፡- እኔ ለተፈጠሩት ችግሮች መነሻ ነው የምለው ኢሕአዴግ አምባገነን መንግሥት መሆኑ ነው፡፡ ባለፉት የምርጫ ወቅቶች ትክክለኛና ፍትሕዊ ምርጫ አለማካሄዱ፤ የፍትሕና የሌሎችም አካላት ነጻ አለመሆን፤ የፓርቲና መንግሥት መቀላቀል፤ የሚዲያው ነጻ አለመሆን እንዲሁም የመንግሥት ወይም የአንድ ፓርቲ አገልጋይ መሆን፤ ህብረተሰቡ ራሱ በመረጠው መንግሥት ለመተዳደር አለመብቃቱ፤ ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ ፖሊሲ የሌለውና ተቀባይነት ያጣ መንግሥት እየመራ በመምጣቱ ነው ችግሩ የተከሰተው፡፡ እነዚህና ሌሎችም ተደማምረው ለሚታዩት ግጭቶች ምክንያት ሆነዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ውጥረትና ግጭቱን እያባባሰ ያለው የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ነው፤ ፓርቲያችሁ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ያለው አቋም ምንድን ነው?
አቶ ዓምዶም፡- በአጎራባች አካባቢዎች የሚገኙት የኢሕአዴግ እህት ድርጅቶች (አዴፓና ህወሓት) ያላቸውን የሥልጣን ሽኩቻ መሬት ማስያዝ ይፈልጋሉ፡፡ ጥያቄ እንዳይነሳባቸው የተለያዩ ሴራዎችን ይሠራሉ፡፡ እኛ እንደ አረና ሕገ መንግሥቱ ያጸደቀውን የአከላለል ሂደት እንከተላለን፡፡ በወልቃይትም በራያም ያለው ትግርኛ ተናጋሪ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት በትግራይ ክልል መሆኑን ነው የተቀበልነው፡፡ ጥያቄ ካለም በዴሞክራሲያዊ መንገድ መጠየቅና መመለስ አለበት ነው የምንለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአረና በኩል መፍትሄው ምንድነው መሆን ያለበት ተብሎ ይታሰባል?
አቶ ዓምዶም፡- ለችግሮቹ መፍትሄው ነው የምንለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ነጻና ገለልተኛ ሆነው ለህብረተሰቡ ቀርበው ፍላጎታቸውንና ያላቸውን አማራጭ አቅርበው በእነርሱ የተመረጠ ሥልጣን ያለው መንግሥት እንዲመሰረት ማድረግ ነው፡፡ እኛ እንደ ዓረና እንደ መድረክም የኢትዮጵያን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ፖሊሲዎች አሉን፡፡ እነዚህ ፖሊሲዎች ቢተገበሩ የኢትዮጵያ ችግር ይፈታል ብለን እናምናለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ህወሓት በምን አይነት አቋም ላይ ይገኛል ብሎ ነው ዓረና የገመገመው?
አቶ ዓምዶም፡- ህወሓት ከፌዴራል ተሸንፎ ነው የመጣው፤ በጣም ችግር ላይ ነው ያለው፡፡ የቆየው በጠመንጃ፣ በደህንነት፣ በፖሊስ እና በገንዘብ ኃይል ሲሆን፤ የትግራይን ሕዝብ ፍላጎት የማያሟላና ለማስተዳደር የማይበቃ ድርጅት ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ተጋልጦ ከፍተኛ አደጋ ላይ ነው ያለው፡፡ ህወሓት የትግራይን ሕዝብ ወደ ጦርነት የሚያስገቡ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያደረገ ነው፡፡ በአማራው ክልል አዴፓ እና በህወሓት መካከል ያለው የሥልጣን ሽኩቻ የሁለቱን ክልሎች ሕዝቦች ያጋጫል፤ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል ብለን እንገምታለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ አክቲቪስቶች፤ እንዲሁም ግለሰቦችና ቡድኖች የትግራይን ሕዝብ ከኢትዮጵያ የመነጠል እንቅስቃሴና ሕዝብን ከሕዝብ የማጋጨት ቅስቀሳ ያደርጋሉ፡፡ በእናንተ በኩል ይሄንን እንዴት ነው የምታዩት?
አቶ ዓምዶም፡- እኛ የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ምንም አይነት ጥያቄ የሚነሳበትና የሚያነሳም ሕዝብ አይደለም ብለን ነው የምናምነው፡፡ አንዳንድ አካላት ግን ለፖለቲካዊ ዓላማቸው እየተጠቀሙበት ነው፡፡ በሀገራችን ያለውን አለመረጋጋት፤ በተለይ በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት መሰረት አድርገው፤ በብሔራችን ብቻ ነው ለይተው እያጠቁን ያሉትና ከእነዚህ ጋር መኖር አንችልም የሚል ግፊት እያደረጉ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የትግራይ ሕዝብ ሀገሩን ትቶ ወደየትም አይሄድም፡፡ እኛ ለዴሞክራሲ፣ ለፍትህና ለሰላም እንታገላለን፡፡ ከትግራይ ሕዝብ ጎን ሆነን ጉዳት እንዳይደርስበት እንዳይበደልና ወደተሻለ ሕይወት እንዲሸጋገር የበኩላችንን ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ህብረተሰቡም በተቻለው መጠን የእነዚህ ውዥንብር ነዢዎች ሰለባ እንዳይሆን ጥረት እያደረግን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች ጥቃት እየደረሰባቸው ነው የሚለውን ሃሳብ ትጋራላችሁ፤ በዚህ ላይ ምን አይነት አቋም አላችሁ?
አቶ ዓምዶም፡- እኛ ከሦስት ዓመት በፊት ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች በትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃቶች እየደረሱ ነበር በማለት ስንታገል ነበር፡፡ ይሄንን በጽኑ ነው የምንቃወመው፡፡ ዜጎች በሀገራቸው በየትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሰው ሠርተው የመኖር መብት አላቸው፡፡ ይሄ እንዲከበርላቸው እንፈልጋለን፡፡ ሰብዓዊ ክብራቸው፣ ንብረታቸው፣ አካላቸው፤ ያፈሩት ሀብት ሳይነካ በማንኛውም ሁኔታ እንዲኖሩ እንፈልጋለን፡፡
የትግራይ ተወላጆች በአማራ፣ በኦሮሚያና በሌሎችም ክልሎች ጥቃት እየደረሰባቸው ነውና ይሄን ጉዳይ በጽኑ ነው የምንቃወመው፡፡ ህወሓት ግን ይሄን ነገር ይፈልገዋል፡፡ ምክንያቱም እኔ ከሌለሁ ያጠፉሀል የሚል ፕሮፖጋንዳ በመሥራት ይጠቀምበታል፡፡ በጽሑፍ አይንጸባረቅም እንጂ ውስጥ ውስጡን ይጠቀምበታል፡፡ እኛ ግን ከሰላማዊ ሰልፍ ጀምሮ የተለያዩ እቅዶች በማውጣት ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር በመነጋገርና ዲፕሎማሲያዊ ትግል በማድረግ ጥቃቱ እንዲቆም ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ይሄን ደግሞ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሊደግፈውና ሊረዳው የሚገባው ጉዳይ ነው ብለን እናምናለን፡፡
ህወሓቶች ሕገ መንግሥት ይከበር የሚል ሰልፍ ወጥተው ነበር፡፡ ጥቃቱ ወደ ባለሥልጣናት ማነጣጠር ሲጀምር ነው እንዲህ ማለት የጀመሩት፡፡ በተግባር ግን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ሲፈናቀሉና በተለይ ለጥቃት ሲዳረጉ ምንም አይነት የተቃውሞ ድምጽ ለማሰማት ጥረት አልተደረገም ነበር፡፡ እኛ ግን እየታገልነው ነበር ለማለት እችላለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በመርሕ ደረጃ የየትኛውም ብሔር ተወላጅ ከሚኖርበት ሲፈናቀል መቃወም ይገባል፡፡ በዚህስ ላይ ምን ይላሉ ?
አቶ ዓምዶም፡- እኛ በየትኛውም የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚደርሰውን ጥቃትና መፈናቀል እናወግዛለን፡፡ በሁለት መንገድ ነው የምናወግዘው – አንዱ እንደ ዓረና፤ አንዱ እንደ መድረክ፡፡ ሰፋ ያለ ሲሆን፣ በመድረክም ውስጥ ባለን ቦታ ተቃውሟችንን እንገልጻለን፡፡ ለትግራይ ተወላጆች ብቻ አይደለም፡፡ በአማራም፣ በሶማሌም በኦሮሞም ብሔረሰብ …እንዲህ አይነቱ ጥቃት ሲፈጸም ከመድረክ ጋር በመሆን ከመጀመሪያው ጀምረን በጽኑ ስንቃወምና ስንታገል ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከሌብነትና ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩና በማዕከላዊ መንግሥት የሚፈለጉ ግለሰቦች ትግራይ ክልል ገብተው መሽገዋል ይባላል፡፡ ይህን አይነቱን ሁኔታ የትግራይ ሕዝብ ይቀበለዋል ብለው ያምናሉ ? የድርጅታችሁስ አቋም ምንድነው?
አቶ ዓምዶም፡- በይፋ ባይገለጽም የተወሰኑ ሰዎች የፍርድ ቤት ማዘዣ ወጥቶባቸዋል እየተባለ ነው፡፡ አንዱ ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ነበሩ፡፡ እርሳቸው ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡ ኢሕአዴግ ሙስናን የፖለቲካው መሸፈኛ አድርጎ ይጠቀምበት ነበርና ካለፈው ታሪክ ተነስተው ብዙ ሰዎች ጥርጣሬ አድሮባቸዋል፡፡ ይህን ጥርጣሬያቸውን የሚያጠናክረው ደግሞ በወቅቱ የነበሩት ኃላፊዎች በሙሉ አለመጠየቃቸው ነው፡፡ የቦርድ ኃላፊዎች የውሳኔው አካል ነበሩ፤ ከእነርሱ እውቅና ውጪ ውሳኔ አይሰጥም ግን አልተጠየቁም የሚለውን የህወሓት ሰዎችም ያነሳሉ፡፡ እነርሱ ያልተጠየቁት በፖለቲካዊ ምልከታቸው ነው የሚሉ ጥርጣሬዎች አሉ፡፡
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በወንጀል ከተጠረጠረ ተከሶ ሕግ ፊት ቀርቦ ወይ ወንጀለኛ ወይ ነጻ መባል ያለ ነውና፤ ሌላ ተጽዕኖ እንዳያሳድር በጥንቃቄ እነዚህ ነገሮች ቢደረጉ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ ለህወሓት ፕሮፓጋንዳ የተመቹ ነገሮች አሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በትግራይ የፖለቲካ እስረኞች አሉ የሚል ቅሬታ በተደጋጋሚ አሰምታችኋል፤ በሌሎች ክልሎች እስረኞች ሲፈቱ ያልተፈቱበት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ዓምዶም፡- በአገሪቱ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ታስረው የነበሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈተዋል፡፡ በትግራይ ግን እስካሁን አልተፈቱም፡፡ በእስር ላይ የሚገኙ ሦስት የዓረና አባላት አሉን፡፡ የደምህት አባላት ደግሞ በርካታ ናቸው፡፡ ይሄ የሚያሳየው ኢሕአዴግ ወጥ የሆነ እንቅስቃሴ አለማድረጉንና በተለይም ትግራይ የለውጡ አካል እንዳልሆነ ነው፡፡ አባሎቻችንም ይሁኑ የደምህት አባላትም ሊፈቱ አልቻሉም፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩም አልሰፋም፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን በሀገሪቱ በተጨባጭ ያለውን እንቅስቃሴና ለውጥ ዓረና ፓርቲ እንዴት ይመለከተዋል ?
አቶ ዓምዶም፡- ለውጡ መልካም ነው፡፡ ዓረና እንደ ዓረናም እንደ መድረክም የምርጫ ፓርቲ በመሆናችን ተወዳድረን አሸንፈን የኢትዮጵያን መንግሥት በመመስረት ችግሮች ሊፈቱ ይገባል፡፡ ዓረና የፖለቲካ ምሕዳሩን የሚያሰፉ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ይፈልጋል፡፡ ሚዲያው ነጻ እንዲሆን፤ መንግሥታዊ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዲቆሙ የመንግሥት ተቀጥላ ወይም የፓርቲ መሣሪያ ሆነው እንዳይቀጥሉ፤ሚዲያው ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩልነት የሚጠቀሙበት መሆን እንዳለበት ሥልጣን የያዘ አካል ብቻ ሆኖ አላሠራም እንዳይል እንፈልጋለን፡፡
በተለይ እንደ ምርጫ ቦርድ የመሰሉ ተቋማት ደግሞ በጣም ነጻና ገለልተኛ በሆነ መንገድ እንዲመሩ እንዲዋቀሩ እስከ ወረዳ ባለው ሁኔታ እስከ ድምጽ ምርጫ ጣቢያዎች ድረስ ሄዶ የፖለቲካ ፓርቲዎችም አማራጫቸውን የሚያቀርቡበት እንዲሆን ነው የምንፈልገው፡፡ እንደ በፊቱ ኮሮጆ ይዘረፋል አይዘረፍም የሚል ስጋትም እንዳይኖር እንፈልጋለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- በእነ ዶክተር አረጋዊ በርሄ ከሚመራው (ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር/ትዴት) ፓርቲ እና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ያደረጋችሁት ስምምነት በምን መልኩ እየሄደ ነው?
አቶ ዓምዶም፡- ከትዴት ጋር አብረን ለመሥራት የመጀመሪያ ስምምነት አድርገናል፡፡ በፕሮግራማችንና በፖሊሲዎቻችን ላይ እየተወያየን ነው፡፡ ያሉንን ልዩነቶች አጥብበን ወደ አንድ ለመምጣት ወይ በግንባር ደረጃ ለመሥራት፤ ከቻልን ደግሞ ወደ ውህደት ለመምጣት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ሌሎችም ወደ ሀገር ቤት የገቡ ፓርቲዎች ስላሉ አብረን ለመሥራት ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡ ከሌሎችም በፕሮግራም ከእኛ ጋር ከሚመሳሰሉ አገር አቀፍና ክልላዊ ፓርቲዎች ጋር በመድረክ ደረጃም ቢሆን አብረን ለመሥራት ዝግጁ ነን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለትግራይ ሕዝብ ከህወሓት የተለየ ምን ፖሊሲና አማራጭ አላችሁ?
አቶ ዓምዶም፡- ከትግራይ ሕዝብ ፍላጎትና የኑሮ ሁኔታ እንዲሁም በተፈጥሮ የተሰጡትን ሀብቶች መሰረት ያደረገና የህብረተሰቡን ኑሮ ከፍ ወዳለ ደረጃ ለመለወጥ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን ቀርጸን ነው እየተንቀሳቀስን የነበርነው፡፡ ይሄም ከፍተኛ ድጋፍ ሲያስገኝልን ነበር፡፡ ይሄንን በሚዲያ፣ በአካልና በስብሰባም አቅርበን ተወያይተን የሕዝብ ሀሳብና ፖሊሲ ሆኖ አሸንፎ እንዲወጣ ነው ጥረት እያደረግን ያለነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አመሰግናለሁ !
አቶ ዓምዶም፡- እኔም አመሰግናለሁ !