• በ5 ወራት 30 ትራንስፎርመሮች ተሰርቆበታል
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅት በ2011 ዓ.ም 10 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ይፋ ቢያደርግም ከግንቦት ወር ወዲህ ከ30 በላይ ትራንስፎርመሮች ተሰርቀዋል።ድርጅቱ ከመጪው ታህሳስ ወር ጀምሮ የታሪፍ ማሻሻያ እንደሚያደርግ የአገልግሎቱ ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አስታውቀዋል።
ዳይሬክተሩ አቶ መላኩ ታዬ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2011 አፈጻጸምና በ2012 ዕቅድ ዙሪያ መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ ከኢነርጂ ሽያጭ፣ ከውዝፍ ሂሳብ እና ከማያገለግሉ ንብረቶች ሽያጭ 21 ነጥብ 868 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 10 ነጥብ 123 ቢሊየን ብር ሰብስቧል።
አፈጻጸሙ ከእቅዱ አንጻር 46 በመቶ ብቻ መሆኑን ያነሱት አቶ መላኩ በቀጣይ ዓመት የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል።በበጀት ዓመቱ በዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ሲከናወን የነበረው የስምንት ከተሞች የማሰራጫ መስመር ማሻሻያና አቅም የማሳደግ ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የስድስት ከተሞች የማሰራጫ መልሶ ግንባታና አቅም የማሳደግ ፕሮጀክት 27 በመቶ መድረሱን ገልፀዋል።
እንደ አቶ መላኩ ማብራሪያ፤ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ እየደረሱ ያሉ ስርቆቶችና አደጋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከግንቦት ወር ወዲህ ባሉት አምስት ወራት ብቻ 30 የሚደርሱ ትራንስፎርመሮች ተሰርቀዋል።በመሆኑም የመሠረተ ልማት ስርቆቱ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል።ስርቆቱ በክሬን ጭምር የታገዘ እንደነበር አንስተዋል።
የትራንስፎርመር ስርቆት ተቋሙ ያልተቆራረጠና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት ለሚያደርገው ጥረት አንዱ ፈተና ሆኗል ያሉት አቶ መላኩ በቴክኖሎጂ በመደገፍ ወንጀሉን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።ህብረተሰቡም ወንጀሉን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በማገዝ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከመጪው ታህሳስ ወር ጀምሮ የህብረተሰቡን የመክፈል አቅም ባገናዘበ መልኩ የታሪፍ ማሻሻያ ተግባራዊ ይደረጋል።የታሪፍ ማሻሻያው በዋናነት አገልግሎቱን የተሻለ ለማድረግ በማሰብ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ህብረተሰቡ ይህንን ሊረዳ ይገባል ብለዋል።የታሪፍ ማሻሻያው ተቋሙ ቢያንስ ወጪውን መደጎም በሚያስችል ደረጃ እንዲሆን ታስቦ ተግባራዊ የተደረገ ነው ብሏል።የታሪፍ ማሻሻያው የሀይል አጠቃቀምን መሰረት ያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
የታሪፍ ማስተካከያው ባለፈው ዓመት የጸደቀ ሲሆን ጫና ላለማሳደር ሲባል በአራት ዓመት ተከፋፍሎ ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኑ የሚታወስ ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2012
መላኩ ኤሮሴ