በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ደንዲ ወረዳ የሚገኙት የዋሙራ ሰቆ ቀበሌ አርሶ አደሮች በሬን ከእርሻ እና ከውቂያ እራሳቸውንም ከአረም እና ከአጨዳ የሚገላግላቸውን ቴክኖሎጂ እየተላመዱ ነው።ስንዴ በማሽን እየታጨደና እየተወቃ ምርቱ በጆንያ ሲሰበሰብ ይህን ምርት የሰጠ መሬት ደግሞ እግር በእግር በትራክተር እየታረሰ ሌላ ሰብል ሲዘራበት ከማየት በላይ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ያስደሰታቸው ያለ አይመስልም።
አርሶ አደር ስሜ ሄዪ በግብርና ህይወታቸው አዲስ ምዕራፍ እንደጀመሩ ይናገራሉ።አቶ ስሜ በአካባቢው የኩታ ገጠም አስተራረስ ግንዛቤ ካገኙ ሀምሳ ስድስት ወሰንተኛ አርሶ አደሮች ጋር በመቀናጀት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በባለሙያ በመታገዝ ግብርናውን በአዲስ መልክ እያስኬዱት መሆናቸውን አስረድተዋል።አቶ ስሜ በግብርና ህይወታቸው ያሳለፉትን መለስ ብለው ሲያዩት ቁጭት እንደፈጠረባቸው ይገልጻሉ።
የግብርና ባለሙያዎች ኩታ ገጠም መሬቶችን አንድ ላይ ማልማት ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚያስገኝ ሲነግሯቸው ለጊዜው እንዳልመሰላቸው የተናገሩት አርሶ አደሩ አሁን ግን ባዩት ውጤት እጅግ በጣም ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ።በቀበሌው በኩታ ገጠም እርሻ ተደራጅተው የሚሰሩ በርካታ ቡድኖች ውጤታማነታቸው ባያጠራጥርም የእነ አርሶ አደር ሄዪ ቅንጅት ግን ለአካባቢው አርሶ አደር ሁሉ ተጠቃሽ ሆኗል።
የእርሻ መሬታቸው ጥቁር አፈር /ኮቲቻ/ በመሆኑ በተለይ ስንዴን ማምረት እንደማይቻል የሚናገሩት አርሶ አደሩ በግብርና ባለሙያዎች በመታገዝ ጥቁር አፈርን አጠንፍፎ የመዝራት ቴክኖሎጂን በመተግበር ስንዴን ማምረት መቻላቸውን አስረድተዋል።
ባልተለመደ ሁኔታ በሄክታር የሚያመርቱት ምርትም በእጥፍ መጨመሩን ይናገራሉ።የግብርና ግብዓቶችንና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀማቸውም ለገበሬውም ሆነ በእርሻ ሥራው ላይ ለሚሰማሩ እንስሳት እፎይታን የሰጠ እንደሆነና የጊዜ፣ የጉልበትና የመሬት ብክነት ሳይኖር ማምረት መቻሉን አስረድተዋል።
በተለይ ጥቁር አፈር ውሃን የመያዝ ባህሪ ያለው በመሆኑ ስንዴው ከማሳው ላይ እየታጨደ ተወቅቶ ምርቱ በመሰብሰብ ላይ እያለ እግር በእግር በመሬቱ በትራክተር እየታረሰ ሽንብራ መዝራት መቻሉ ቴክኖሎጂው ምን ያህል ጥቅም እየሰጠ እንዳለና ለነገ የሚባል ሥራ እንደሌለ አስረድተዋል።
የልማት ሙያተኛው ወጣት ዴቢሳ ኮሬ በበኩሉ እንደሚገልጸው በ86 ሄክታር ኩታ ገጠም መሬት ላይ ለተዘራው ስንዴ ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይገልጻል።አርሶ አደሩ የባለሙያውን አስተያየትና ምክር በመቀበል የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆኑ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አግዟል ይላል።
በአንድነት ማህበር 48 ወንዶችና 8 ሴቶች በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ መደራጀታቸው የተለያዩ የቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ አስችሏቸዋል ይላል።ከዚህም በተጨማሪ የጉልበት ፣ የበሬ ፣የዘር ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል አደረጃጀት እንደሆነም ተናግሯል።
በአንድ ጀንበር የደረሰውን አዝመራ የማጨድ፣ አዲስ ዘር የመዝራት እና መሰል ቀልጣፋ ተግባራትን የማከናወን አመቺነት እንዳለውም ገልጧል።ይህ አሰራርም በዓመት ሁለት ጊዜ የማምረት ዕድል እንደሚሰጥ ባለሙያው ገልጧል። ስንዴው እየታጨደ ከስር ከስር ሽንብራ መዝራት ያለው ጠቀሜታም ሽንብራ እምብዛም ውሃ ስለማይፈልግ መሬቱ በያዘው እርጥበት ብቻ ውጤት እንደሚገኝበት በማስተማር ነው ይላል።
አቶ ከበደ ደበሎ በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሸዋ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ እንደሚያስረዱት የ2011/12 የምርት ዘመንን ውጤታማ ለማድረግ ሰፊ ቅስቀሳና ድጋፍ ሲደረግ እንደነበር አስታውሰው መሬትን በተመሳሳይ ምርት የመሸፈን ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።
በመሆኑም ኩታ ገጠም መሬቶችን በተመሳሳይ ሰብል ማለትም በጤፍ፣ በስንዴ በቆሎ በመሳሰሉት ለመሸፈን ዞኑ ባለፈው ዓመት የእቅዱን 82 በመቶ ማሳካት መቻሉን እና ወደ 190 ሺ አርሶ አደሮች መታቀፋቸውን አስረድተዋል።ይህም አርሶ አደሮቹን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸውና የአካባቢው ምርታማነትም እንደጨመረ ገልፀዋል።
ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን መጠቀም ምርታማ ማድረጉን ተከትሎም በአካባቢው ከሚገኙ ህብረት ሥራ ማህበራት ጋር በመነጋገር ምርቱ ከመሰብሰቡ በፊት የገበያ ትስስር መፈጠሩን ኃላፊው ተናግረዋል።በዞኑ ባሉ 22 ወረዳዎች የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ ተግባራዊ እየተደረገ እንዳለ አቶ ከበደ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2012
ኢያሱ መሰለ