‹‹ቆሻሻ ሀብት ነው። አያያዙ ነው ቆሻሻ የሚያሰኘው። ለተለያየ አገልግሎት የሚውለው ኬሚካልም ለሚፈለገው ብቻ እንዲውል ካልተደረገ ክምችቱን ለማስወገድ የሚወጣው ወጪ የሀገር ኢኮኖሚን ይጎዳል›› ይላሉ በአካባቢ የአየር ንብረትና ለውጥ ኮሚሽን የደረቅና አደገኛ ቆሻሻ አያያዝ ህግ ተከባሪነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ገመቹ።
እንቅስቃሴው በኢኮኖሚው ውስጥ በምን ያህል አስተዋጽኦ እንዳበረከተ በጥናት ባይለይም በሥራ ዕድል ፈጠራና በሥራ ላይ ካሉት ፕሮጀክቶች አንጻር አበረታች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መኖሩንና የበለጠ ለመስራት ተስፋ ሰጭ እንደሆነ በመጠቆም ከሚመነጨው የቆሻሻ መጠን አንጻርም የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ተናግረዋል።
የግሉ ዘርፍ ጥቅም ላይ ውለው የተጣሉ ብረታብረትና ፕላስቲኮች መልሶ በመጠቀም ለግንባታና ለተለያዩ አገልግሎቶች በማዋል በስፋት በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነ፣ በአሁኑ ጊዜም በአዲስ አበባ ከተማ ከ20 በላይ የፕላስቲክ፣ ስድስት የብረታብረት መልሶ መጠቀም ድርጅቶች መቋቋማቸውን፣ በአጠቃላይ በከተማዋ 30ሺ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩንና በአዲስ አበባ ከተማ ብቻም ስድስት ሺ አንድ መቶ ወጣቶች እሴት ሳይጨምሩ ቆሻሻን በመሰብሰብ ተጠቃሚ መሆናቸውን አቶ ግርማ አስረድተዋል።
ኬሚካልን በተመለከተም እንዳብራሩት የሚፈለገውን ብቻ ለይቶ መጠቀም ካልተቻለ ጉዳቱ ዘላቂና ለማስወገድም ከፍተኛ ገንዘብ ይጠይቃል። በአንድ ወቅት ለወባ መከላከያ ተብሎ የተገዛ ‹ዲዲቲ› የተባለ ጊዜ ያለፈበትን ኬሚካል ለማስወገድ ከሦስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ መጠየቁን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በተመሳሳይ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ኬሚካሎች መኖራቸውንም አመልክተዋል። እንደግብርና ጤና፣ ትምህርት ያሉ በስፋት ኬሚካል የሚጠቀሙ ተቋማት መለየታቸውንና ከችግሩ ስፋት አኳያ ለማስወገድ ከፍተኛ መሰረተ ልማት የሚፈለግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ባለው የህግ ማዕቀፍም ሳይፈታ መቆየቱን ይገልፃሉ።
በኮሚሽኑ የፍሳሽ ቆሻሻ የህግ ተከባሪነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ኃይለየሱስ እንዳብራሩት በኢትዮጵያ በሚሌኒየም የልማት ግብ መሰረታዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ማሟላት፣በዘላቂ ልማት ግብ ደግሞ ፍሳሽ ቆሻሻን አክሞ ለተለያዩ አገልግሎቶች በማዋል መጠቀም የሚል ዕቅድ ቢነደፍም የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም። ችግሩ በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ላይ እንደሚስተዋልና የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃና ማከሚያ ሥርዓት ባለመኖሩ 80 በመቶ የሚሆነው ፍሳሽ ቆሻሻ በቀጥታ ወደ አካባቢ እንደሚለቀቅ ገልጸዋል።
ቆሻሻን መልሶ ለማዳበሪያ፣ለኃይል ምንጭና ለተለያየ ጥቅም እንዲውል፣ካልተቻለ ደግሞ ቆሻሻ በአግባቡ በማጓጓዝ በተገቢው ቦታ በማስወገድ ጉዳቱን መቀነስ እንደሚገባ በአካባቢ ፖሊሲው ላይ መስፈሩን ያወሱት አቶ ሰለሞን፣በአንዳንድ ከፍተኛ ትምህርትና ጤና ተቋማት ከመመገቢያና ከተለያዩ ክፍሎች የሚወገዱ ፍሳሽ ቆሻሻዎችን በመሰብሰብ በአግባቡ በማስወገድና አክሞ በመጠቀም ለአካባቢ ጥበቃ የሚያደርጉት ጥረትና እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን አመልክተዋል።
በዚህም የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለአሳ ማርቢያ፣ ለአትክልትና ለግብርና ሥራ ከፍሳሽ ቆሻሻ ውሃ 336ሺ ኪዩቢክ ሜትር ማጣራት በመቻሉ በመልካም አንስተዋል። ሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታልና ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲና ሌሎችንም ለአብነት ጠቅሰዋል። በአንዳንዶቹ ላይ መስተካከል ያለበት ነገር መኖሩን አመልክተዋል።
የከተማ አስተዳደሮችም ከየአካባቢያቸው ምን ያህል ፍሳሽ ቆሻሻ እንደሚመነጭና እንዴት መጠቀም እንደሚቻል በእቅድ እንደማይመሩና የአቅም ውሱንነት እንዳለባቸው ኮሚሽኑ እንደደረሰበት የጠቆሙት አቶ ሰለሞን፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመስራትና የጋራ ዕቅድ በማውጣት እንዲሁም ግንዛቤ በመፍጠር፣ አቅም በመገንባትና በጥናት በመደገፍ በዘርፉ ውጤት ለማስመዝገብ ኮሚሽኑ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክክሩ ከትምህርትና ከጤና ተቋማት ጋር በቅድሚያ መደረጉ የምርምር ሥራዎች የሚያከናውኑ በመሆናቸው፣ከሚያስተናግዱት የሰው ብዛት አንጻርም ጥሩ የሆነ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት እንዲዘረጉና የተሻለ ቴክኖሎጂ ፈጥረው ጥቅም ላይ ለማዋል እድሉ ስላላቸው ጭምር እንደሆነና አካባቢያቸውን ማገዝ እንደሚችሉም በመታመኑ በአካባቢ የአየር ንብረትና ለውጥ ኮሚሽን የአካባቢ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ ያስረዳሉ።
ኮሚሽኑ በተሰጠው ስልጣንና ተግባርም በተቋማቱ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ክትትልና ቁጥጥር ማድረጉንና በዚሁ መሰረትም ጠንካራውን ለማጎልበት ውስኑነቶችም እንዲቀረፉ እና በጋራም ለመስራት ምክክሩ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
ዋናው ተግዳሮቶች የግንዛቤ ችግር እንደሆነ በኮሚሽኑ መታመኑን የጠቆሙት ወይዘሮ ፍሬነሽ ግንዛቤ በመፍጠር ደረጃ በደረጃው የወጡ ህጎች፣ መመሪያና ደንቦች እንደሚተገበሩ ገልጸዋል። እኤአ በ2030 ከተሞች 50 በመቶ ቆሻሻ በአግባቡ እንዲያስወግዱና እንዲጠቀሙ ግብ መጣሉን ኮሚሽነሯ ያስታውሳሉ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2012 ለምለም መንግሥቱ