አዲስ አበባ፡- በዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ጽህፈት ቤት በኢትዮጵያ ሥራ ጀመረ። ጽህፈት ቤቱ በአህጉሩ ውስጥ እንዲሰራ መደረጉ የአፍሪካ ሀገራትን የሚቲዮሮሎጂና የሀይድሮሎጂ አገልግሎቶችን ለማቀናጀት አቅም እንደሚፈጥር ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ፈጠነ ተሾመ ጽህፈት ቤቱ በኤጀንሲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ድርጅቱ ትናንት ሥራውን በይፋ መጀመሩን አስመልክቶ በተከናወነው ልዩ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ጽህፈት ቤቱ ወደ አህጉሩ እንዲመለስ በኢትዮጵያ መንግሥትና በዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት መካከል ከሁለት ዓመት በፊት በተደረገው የፊርማ ስምምነት መሰረት ተፈጻሚ ሆኖ በይፋ ሥራ መጀመሩን ለማብሰር የተከናወነ ሥነ ሥርዓት መሆኑን አመልክተዋል።
ጽህፈት ቤቱ ለረጅም ዓመት ቡሩንዲ ውስጥ ሲሰራ እንደነበርና በሀገሪቱ በተፈጠረው የእርስ በርስ ጦርነት የተባበሩት መንግሥታት መቀመጫ በሆነው ጄኔቫ ውስጥ መቆየቱን አስታውሰው፣ከብዙ ውይይት በኋላ ስምንት የአፍሪካ ሀገራት ተወዳድረው ጽህፈት ቤቱ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰራ መወሰኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት አባል ሀገር እንዲሁም የአፍሪካ እና የተለያዩ ዲፕሎማቶች መቀመጫ መሆኗ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተደራሽነትና ሌሎችንም መስፈርቶች አሟልታ በመገኘቷ ተቋሙ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሆን አድርጓል ብለዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተጋበዙት የውሃና መስኖ ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት በጤና፣ በትራንስፖርት፣ በግብርን ዘርፍና በሌሎችም ፋይዳ ያለው አገልግሎት እንዳለው አውስተው፣ የፖለቲካ ድንበር የሌለውን ይህን አገልግሎት በትብብር መስራት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።በዘላቂ የልማት ግብ ረሃብን ዜሮ ለማድረስ ለሚደረገው ጥረት አገልግሎቱን ማዘመን እንደሚገባና ኢትዮጵያም አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የሚጠበቅባትን እንደምትወጣ ገልጸዋል።
የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፕሮፌሰር ፒተር ታለስ በበኩላቸው አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጭ ተጋላጭነቷን ለመቀነስም ሆነ በተለይም ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጥረትና እየተፈታተናት ላለው የአየር ንብረት ለውጥ ጽህፈት ቤቱ በአህጉሪቱ ውስጥ መስራቱ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2012
ለምለም መንግሥቱ