አዲስ አበባ፡- በሶስት ቋንቋዎች በመደመር እሳቤ ላይ የተጻፈውና ‘‘መደመር’’ የተሰኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ መጽሐፍ የፊታችን ቅዳሜ ጥቅምት 8 ቀን 2012 እንደሚመረቅ ተገለፀ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ትናንት የመጽሐፉን ምረቃ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የመደመር እሳቤን በተመለከተ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጻፈው መጽሐፍ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ነው።
እንደ አቶ ንጉሱ ማብራሪያ፤ መጽሐፉ በ1 ሚሊዮን ኮፒ ተዘጋጅቶ በሁሉም የአገሪቷ ክልሎች እየተሰራጨ ሲሆን፣ የህትመት ሥራው በአሜሪካና ኢትዮጵያ ማተሚያ ቤቶች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ታትሟል። የመጽሐፉ የእንግሊዝኛ ዕትም ከሶስት ወር በኋላ ለአንባቢያን ይደርሳልም ተብሏል፡፡
ጥቅምት 8 ቀን 2012 ዓ.ም አዲስ አበባን ጨምሮ በ20 የሀገሪቱ ከተሞች ላይ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ለምረቃ እንደሚበቃ በመግለጫው የተነገረ ሲሆን በውጭ በዋሽንግተን፣ ሎስአንጀለስ፣ ሚኒሶታ እና ናይሮቢ ከተሞች እንደሚመረቅም ተገልጿል።
መጽሐፉ ለምረቃ ከበቃ እና አንባቢያን እጅ ከገባ በኋላ ይዘቶቹ ለህብረተሰቡ ግልፅ የሚደረጉ ሲሆን፣ ይህን መሰረት አድርገው ተንታኞች ይዘቶቹን በየርዕሱ እየተነተኑ ሀሳብ የሚያቀርቡበት፣ የሚመረምሩበትና የሚተቹበት መድረኮች ተዘጋጅተው ሀሳብ የሚለዋወጡበት እንደሚሆንም አቶ ንጉሱ ተናግረዋል፡፡
የሀገራችንን ቁልፍ ችግሮች የሚፈቱ እሳቤዎች ተካተውበታል የተባለው መጽሐፉ ባለስልጣናት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በሚገኙበት ይመረቃል፡፡
የየአካባቢውን ባህል መሰረት አድርጎ ምረቃው የሚከናወነው መጽሐፉ 300 ብር ዋጋ የተቆረጠለት ሲሆን ከመጽሐፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በአገሪቷ ውስጥ ትምህርት ቤቶችን ለማሰራት እንደሚውል በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/2012
ድልነሳ ምንውየለት