.እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ይገነባል
.አጋሮችን ከሩቅ ተመልካችነት ወደ ውሳኔ ሰጭነት ያመጣል
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የሚነሱ የፖለቲካ ጥያቄዎችን ለመመለስና ለማስቀጠል ዕውነተኛ የፌዴራል ሥርዓት መገንባት አማራጭ የሌለው መፍትሄ እንደሆነና የኢህአዴግ ውህደት ዋነኛ ዓላማም የፌዴራል ስርዓቱን ማጠናከር እንደሆነ ምሁራን ገለጹ።
የኢህአዴግን ውህደት በማስመልከት በተካሄደው አገር አቀፍ ጥናት የተሳተፉት ረዳት ፕሮፌሰር አንተነህ ሙሉ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ የፌዴራል ሥርዓትን በተመለከተ አሁን ኢህአዴግ አገሪቱ ካለችበት ወይም ከዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም ከውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎች አንጻር ራሱን እየፈተሸ ሪፎርም ሊያካሂድ ይገባል ብለዋል።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር አንተነህ ገለፃ ይህ የፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ የሚታይ ነባራዊ ሁኔታ ሲሆን፤ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ግን እንደ አገር የምንከተለው አካሄድ ነው። ኢህአዴግ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ባለፉት ሩብ ምዕተዓመት ጉልህ ሚና የተጫወተ ፓርቲ ነው። ያ ሚናው ለወደፊቱም የሚቀጥልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል መገመት ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ራሱን እየፈተሸ ማስተካከል የግድ ነው።
የፌዴራል ሥርዓቱ ኢህአዴግ ወይም የሚዋሃደው ፓርቲ ስለፈቀደ ወይም ስለጠላ የሚፈርስና የሚቀጥል አይሆንም የሚሉት አቶ አንተነህ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የሚነሱ የፖለቲካ ጥያቄዎችን ለመመለስ እና ለማስቀጠል የፌዴራል ሥርዓቱ አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ የተደመደመ ነው ብለዋል።
የፌዴራል ሥርዓቱን በማጠናከር ሂደት ውስጥ ህብረብሄራዊ አንድነታችን በመሸርሸር የፅንፈኝነት አዝማሚያዎች በመኖራቸው ይህንን ማስተካከል እንደሚገባ ፤ በህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ከማጠናከር አንጻርም ኢህአዴግ ተገቢውን ሚና መጫወት እንዳለበትና ጠንካራ ትስስር ሊፈጠር እንደሚገባ ረዳት ፕሮፌሰር አንተነህ አመላክተዋል።
ከኢህአዴግ ጋር በአጋርነት የቆዩት አምስቱ ድርጅቶችም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ክልላቸውን ሲያስተዳድሩ እኩል ተሳታፊ ለመሆን ጥያቄ ቢያነሱም ሰሚ በማጣታቸው በአገራቸው ጉዳይ ላይ በጋራ ለመወሰን እድሉን ሳያገኙ መቆየታቸውን እና ውህደቱም ችግሩን ይፈታል ተብሎ ታምኖበት ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቅድመ ምረቃ መርሐ ግብር አስተባባሪ ተመራማሪና መምህር ዶክተር ታደሰ ጃለታ በበኩላቸው ኢህአዴግ ውህደት ለመፈፀም ካቀደ ቢቆይም ጥናቱ ከተጀመረ ግን ሁለት ዓመት መሆኑንና በአሁኑ ወቅትም ጥናቱ ተጠናቆ ውይይት እየተደረገበት እንደሆነ ጠቁመዋል።
ጥናቱ አሳታፊ ነበር ያሉት ዶክተር ታደሰ፤ ይህ የፖለቲካ ድርጅት ጥናት በመሆኑ የየብሄራዊ ድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ መካከለኛ አመራሮችና አባላት የተሳተፉበት እንደሆነና የማህበራዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ጉዳይ ሊጠና በሚችልበት የጥናት ደረጃ ሳይንሳዊ ደረጃውን ጠብቆ እንደተከናወነም ጠቅሰዋል።
የፌዴራል ሥርዓትን ከሚከተሉና ብዝሃነት ካለባቸው 28 የአፍሪካና ሌሎች አገራት ልምድ መቅሰሙን ያስረዱት ዶክተር ታደሰ፤ ከዚህ ባሻገር ኢህአዴግ በተለያዩ ጊዜያት ባደረጋቸው ውይይቶች የነበሩትን ቃለጉባኤዎች ለጥናቱ ማዳበሪያነት መጠቀሙን ገልፀዋል።
በኢህአዴግ ውስጥ ሶስት ዋና ዋና ችግሮች እንደነበሩ በጥናቱ ታይቷል ያሉት ዶክተር ታደሰ፤ አንደኛው የአመለካከት ችግር ሲሆን፤ ኢህአዴግ ይህንን ችግሩን ለመቅረፍ በየጊዜው ግምገማ ሲያደርግ እንደነበር፣ ነገር ግን ችግሩ አለመቀረፉንና ለዚህም ዋናው ምክንያት የአደረጃጀት ችግር ስለነበረበትና ኢህአዴግ አቃፊ ባለመሆኑ የመጣ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ኢህአዴግ የተመሰረተው በአራት ክልሎች ከተውጣጡ ፓርቲዎች ሆኖ አገር የሚመራ ቢሆንም ሌሎቹ ፓርቲዎች በአገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ምንም አይነት ተሳትፎም ሆነ ሚና እንዳልነበራቸው የተናገሩት ዶክተር ታደሰ፤ እነዚህን ችግሮች ሙሉ በሙሉ ለመፍታት አጠቃላይ ችግሮቹን መሰረት ያደረጉ ለውጦችን ማካሄድ አስፈላጊ በመሆኑ ጥናቱ መካሄዱን ተናግረዋል።
ዶክተር ታደሰ የአጋር ድርጅቶች አለመሳተፍ በአንድ በኩል በአገሪቷ የውስጥ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ እንዳይሳተፉ ያደረገ ሲሆን በሌላ በኩል በአገሪቷ የውሳኔ አሰጣጥ ላይ ሳይሳተፉ ነገር ግን ውሳኔውን ተቀብለው የመተግበር ግዴታ ውስጥ እንዲገቡ በማድረጉ በአገሪቷ የውሳኔ ሰጪነት ላይ ያላቸውን ሚና መገደቡን ጠቅሰዋል።
ውህደቱ የብሄር ፓርዎችን ይጨፈልቃል፤ አሃዳዊ ሥርዓት ይፈጥራል፤ የፌዴራል ሥርዓትን ይቃረናል በሚል በተለያዩ ሚዲያዎችና ግለሰቦች የሚነሱ ሃሳቦች የተሳሳቱ መሆናቸውንም ዶክተር ታደሰ ተናግረዋል።
እንደ ዶክተር ታደሰ ገለፃ ጥናቱ የሚዋሃደው ፓርቲ አገሪቷን መምሰል አለበት ይላል። አገሪቷ ምን ትመስላለች ካልን ደግሞ ብዝሃነት ያላት አገር ናት። የባህል፣ የማንነት፣ የቋንቋ ወዘተ ብዝሃነት አለ። ስለዚህ ብዝሃነትን የሚያከብርና ብዝሃነትን የሚያንፀባርቅ ፓርቲ መመስረት የዚህ ውህደት ዋነኛ ዓላማ ጭምር ነው። አገራዊ አንድነትን ለመገንባት ደግሞ ብዝሃነትን የሚያከብር እና ብዝሃነት ላይ የተመሰረተ አንድነት እንደሚከተል ያመላክታል ።
‹‹የኢህአዴግ ውህደት ፌዴራል ሥርዓትን ለማጠናከር እንጂ ለማደብዘዝ አይደለም›› የሚሉት ዶክተር ታደሰ ‹‹እስካሁን በተለያዩ ሥርዓቶች ውስጥ ያልታዩና በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ ያሉ በጎ ነገሮችን ይዞ ይቀጥላል›› ብለዋል።
የተለያዩ ቋንቋዎች በሚነገሩባቸውና የፌዴራል ሥርዓትን በሚከተሉ አገራት ከአንድ በላይ ቋንቋ በብሄራዊ ቋንቋነት እንደሚያገለግል፣ በዚህ ጥናትም ይህ መመላከቱ፣ ጥናቱም ቢያንስ አራት ቋንቋዎች ሥራ ላይ እንደሚውሉ ማሳየቱን ዶክተር ታደሰ አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/2012
ወርቁ ማሩ