አዲስ አበባ፡- የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ የ2019 የኖቬል የሰላም ሽልማት በማሸነፋቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው እና በኢትዮጵያዊነታቸውም እንዲኮሩ እንዳደረጋቸው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አስታወቁ::
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ የወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ፣ዶክተር ዓቢይ በመሸለማቸው በጣም መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣኑን ተረክበው ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ ያሰሙት ንግግር ሊፈፀም ይችላል ብለን ሁላችንም በጉጉት ስንጠብቀው ነበር፣ቃላቸውንም በመጠበቅ በተጨባጭ ወደተግባር የለወጡ መሪ ናቸው›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
ወ/ሮ አበባ ‹‹ተባብረን ከሰራን አገራችንን መለወጥና የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ እንደምንችል ከእርሳቸው መረዳት ችለናል::›› ብለዋል፡፡ ‹‹የሁሉ ነገር መሰረት ሰላም ነው፤ ሰላም ለሴቶች ሲሆን ደግሞ እጥፍ ድርብ ነው፡፡ ሰላም ከሌለ የመጀመሪያ ተጎጂ የሚሆኑት ሴቶችና ህፃናት ናቸው፤ከዚህ አኳያም ሽልማቱ እጅግ የሚያበረታታ ነው፡፡›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
የምክር ቤቱ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው፤ ‹‹በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሸለም ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ለውጥ ከተጀመረ አንድ ዓመት ከመንፈቅ በሆነ ጊዜ ውስጥ አንድ የአገር መሪ ህዝቡን አስተባብሮ በብጥብጥና በሁከት ውስጥ እየታመሰች የነበረችን አገር ወደሰላም ለውጦና በሰላም እሴቶች ላይ ሰፊ ሥራ ሰርቶ ውጤት አስመዝግቦ መታየቱ ለተሰማቸው የደስታ ስሜት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አምባሳደር መስፍን እንዳስረዱት፤የኖቬል ሽልማት መሰጠት ከተጀመረ አንስቶ ከአስር ያላነሱ አፍሪካውያን የሽልማቱ ተቋዳሽ ሆነዋል፡፡ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መስራችና በአፍሪካውያን ዘንድም ትልቅ ስፍራ ያላት አገር እንደመሆኗ ለሰላምም ያደረገችው አስተዋፅኦ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡
ከአገራችን አልፎ በምስራቅ አፍሪካ፣ በቅኝ ለተያዙ አገሮችና ለሌሎችም በሰላሙ በኩል ከፍ ያለ ሚና መጫወቷ ይታወቃል፡፡በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሁሉ አልፋ ዛሬ እንደ አገር በጠቅላይ ሚኒስትሯ የኖቬል የሰላም ሽልማት ስታገኝ ታላቅ ኩራትና ደስታን ያጎናጽፋል፡፡
የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ አበባዬ ገዛኸኝ እና አቶ አቡ ቢርኪ በየበኩላቸው ፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱን በማሸነፋቸው ደስታቸው እጥፍ ድርብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በጎረቤት አገራትም የሰሯቸው የሰላም ሥራዎች በተለይ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ሰላም እንድታወርድ የሄዱበት ጉዞ ውጤታማ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ሲሉ ገልጸው፣ይህ ተግባራቸው ዓለምን በማስደመሙና በሰሩትም ልክ ለዚህ ክብር እንዲበቁ በመደረጋቸው ደስ መሰኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ይህም እንደ ምክር ቤት አባላት ትልቅ ተስፋ እንዲሰንቁ እንዳደረጋቸውም ገልጸዋል፡፡ሽልማቱ ተጨማሪ ሥራዎችን እንዲሰሩ እንደሚያበረታታቸው አመልክተው፣ጠቅላይ ሚኒስትሩን ‹‹እንኳን ደስ አልዎት፡፡›› ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኃላፊነት ከመጡ ወዲህ በርካታ ዓለምአቀፋዊ ሽልማቶችን እና እውቅናዎችን ማግኘታቸው የሚታወስ ሲሆን፣100ኛውን የኖቬል የሰላም ሽልማቱን ደግሞ ከቀናት በፊት ማሸነፋቸው ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2012
አስቴር ኤልያስ