በኢኮኖሚው ዘርፍ በ2012 በጀት ዓመት እንደሚከናወኑ ከሚጠበቁ ተግባሮች መካከል የግብርናውን ምርትና ማርታማነት ማሳደግ የሚለው ይገኝበታል፡፡ዘርፉን ለማዘመን በመስኖና ግብርና መካናይዜሽን ላይ በትኩረት እንደሚሰራ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት በቅርቡ የመንግሥትን ዋና ዋናዎቹን የትኩረት አቅጣጫዎች ለፓርላማው ባቀረቡበት ወቅት አስታውቀዋል፡፡ ግብርናን ለማዘመን ለሚያስችለው መካናይዜሽን የቀረጥ ማበረታቻ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡
የዘርፉ ባለድርሻ አካላትም ይህን የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ በማድነቅ መካናይዜሽን ላይ ማተኮር አማራጭ እንደሌለው ይናገራሉ፡፡በግብርና ሚኒስቴር የግብርና መካናይዜሽን ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ሀብቴ የፕሬዚዳንቷን ንግግር እንደ ግብርና መካናይዜሽን ባለሙያ አድንቀው፣ መንግሥት ለመካናይዜሽን የሰጠውን ትኩረት የሚመለከታቸው አካላትም ሊፈጽሙት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡
ሀገሪቱ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ ራእይ መሰነቋን አቶ ታምሩ ጠቅሰው፣ በ14 ሚሊዮን ጥማድ በሬ እያረሱ ይህን ራእይ ማሳካት እንደማይቻል ያስገነዝባሉ፡፡በበሬ ማረሱ በመካናይዜሽን እየተተካ መሄድ እንዳለበት ጠቅሰው፣ለዚህም የልማት ድርጅቶችና ባለሀብቶች ትኩረት መስጠት አለባቸው ብለዋል፡፡
በምርጥ ዘርና ማዳበሪያ የሚጠበቀው ለውጥ በመካናይዜሽን ሲደገፍ 70 በመቶ የምርት ጭማሪ እንደሚያስገኝ ጥናቶችን ጠቅሰው የተናገሩት አቶ ታምሩ፣ መካናይዜሽን የዘር እና የማዳበሪያ ብክነትን ከ15 እስከ 20 በመቶ እንደሚቀንስም ይገልጻሉ፡፡
በሀገራችን ካሉት ዩኒየኖችና ማኅበራት ውስጥ አራቱ ዩኒየኖች ብቻ ኮምባይነር እንዳላቸው ጠቅሰው፣ በሀገሪቱ ያሉት ትራክተሮች ወደ 118 ገደማ መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡በመካናይዜሽን ወደ 2ሚሊዮን አርሶ አደር ተጠቃሚ እየሆነ እንደሚገኝ ይገልጻሉ ፡፡
አቶ ታምሩ አርሶ አደሩ እያረጀ መሆኑን፣ወጣቱም ወደ ግብርና ለመግባት ዝግጁ አለመሆኑን አመልክተው፣አባት ለልጁ ሞፈሩን ለማውረስ ፈቃደኛ አለመሆኑን ልጁም በአካባቢው እንደማይኖር ይጠቁማሉ፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ግብርና መካናይዜሽን አማራጭ እንደሌለው ይጠቁማሉ፡፡
የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ዋቅጅራ መንግሥት መካናይዜሽን ተግባር ላይ የሚያውል ከሆነ የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እንደሚጨምር ጠቅሰው፣ ለከተሜውም ገበያ በማረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይጠቁማሉ፡፡የፕሬዚዳንቷ ንግግር ከዚህ አኳያ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስም ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባም ይገልጻሉ::
‹‹መካናይዜሽን ጉልበትን፣ጊዜንና ገንዘብን ይቆጥባል፤ምርታማነትንና ጥራትንም ይጨምራል›› የሚሉት አቶ ተስፋዬ፣ የተበጣጠሰ ማሳ አንድ ላይ በማደራጀት በኩታገጠም አብረው እያረሱ እያጨዱ ተመሳሳይ ሰብሎችን በመዝራት ለመሥራት እንደሚረዳ ይጠቁማሉ፡፡ መካናይዜሽን ለእርሻ ብቻ ሳይሆን ለተፈጥሮ ሀብት ለቁም እንስሳትና ለደኑም አስተዋፅኦ እንዳለው ይገልጻሉ፡፡
የፌዴራል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ሥራ አስከያጅ አቶ ዑስማን ሱሩር ግን የቀረጥ ማበረታቻ ለኅብረት ሥራ ማህበራት አዲስ አይደለም ይላሉ፡፡ማኅበራቱ ከቀረጥ ነጻ ማበረታቻን ሙሉ ለሙሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፣በዚህም መካናይዜሽን አገልግሎቱን ከፍ ማድረግ ችለዋል ይላሉ፡፡
እንደ አቶ ኡስማን ገለጻ፣በሀገሪቱ ወደ 860 አካባቢ የሚደርሱ ማጨጃ ፣መውቂያ፣ ማረሻና መከስከሻ የመካናይዜሽን መሣሪያዎች በገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት አገልግሎት እየሰጡ ናቸው፡፡በአማራና ደቡብ ክልሎች አንድ ኩንታል ስንዴ አጭዶ ወቅቶ ለማስረከብ ከ100-135 ብር የነበረውን ክፍያ ማኅበራቱ ባሉበት ግን ከ65-75 ብር ነው፡፡
ማኅበራቱ ባሉበት በአካባቢ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሀብቶች ዋጋውን በአንድ ኩንታል ወደ 85 ብር አውርደዋል፡፡ ማኅበራቱ ባሉበት አካባቢ ያለ አርሶ አደር ከ45-55 ብር ዋጋ ቅናሽ አግኝተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ