አሶሳ፤ የኢህአዴግ ውህደትን ዕውን በማድረግ፣ አምስቱን አጋር ድርጅቶችንም በመቀላቀል ወጥ የሆነ ፓርቲ ተመስርቶ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ችግር በጋራ በመወያየት መፍታት እንደሚገባ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሳሰበ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሌ ሐሰን በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ አምስቱ አጋር ድርጅቶች በአገራቸው ጉዳይ ላይ በጋራ ለመወሰን እንዲችሉ ውህደቱ እንዲፈጠር ጥያቄዎችን ሲያነሱ መቆየታቸውን ጠቁመዋል። በአንድ አገር ውስጥ አንዱ ቤተኛ ሌላው ባይተዋር ሆኖ የቆየበት ሁኔታም ጥሩ አይደለም በሚል ከአጋር ድርጅቶቹ የውህደት ጥያቄ ሲነሳ መቆየቱንም ተናግረዋል።
በድርጅትም ሆነ በፓርላም የተገለሉበት ነገር እንደነበር የገለፁት አቶ አሻድሌ፤ “አጋር ድርጅቶቹ ወደ ግንባሩ መቀላቀል አለብን፣ በዚህ ሂደት ብዙ መብቶች አጥተናል” በሚል ጥያቄ ሲያነሱ እንደነበረም አስታውሰዋል።
እንደ አቶ አሻድሌ ማብራሪያ፤ ኢህአዴግ ከቀረፀው ፕሮግራም አኳያ በየጊዜው ወጥ የሆነ ፓርቲ ለማቋቋም አጀንዳው እየተነሳ ከአምስተኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ጀምሮ ስንወያይበት ቆይተናል። የእኛን ክልል ጨምሮም ምሁራን የተሳተፉበት ከፍተኛ ጥናት ተደርጓል። ጥናቱ ውህደት ይደረግ ወይስ አሁን ባለበት ሁኔታ ይቀጥል የሚለው አጀንዳ አካትቶ ነበር። አብዛኛው ሰው በዚህ መልኩ ባይቀጥልና አጋር ድርጅቶች ተቀላቅለው ወጥ ፓርቲ ተመስርቶ በአገር ደረጃ ያለውን ችግር በአንድነት በመወያየት ሊፈታ ይገባዋል የሚል ምላሽ መገኘቱን አንስተዋል።
አቶ አሻድሌ፤ “አሁን ውይይት ላይ ነን። ወደፊት በጥናቱ ዙሪያ በስፋት ውይይት ሊደረግበት ይችላል። የኢህአዴግ ውህደት ራስን በራስ ማስተዳደር መብትን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ አይሆንም” ብለዋል።
አገሪቱ ባለፉት 28 ዓመታት በአንድ ግንባርና በአምስት አጋር ፓርቲዎች እየተመራች ቆይታለች ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ባለፉት ዓመታትም ፓርቲዎች ባላቸው ፕሮግራም ስትራቴጂዎችን፣ መመሪያዎችን፣ አሠራሮችንና በመንግሥት የሚተገበሩ አቅጣጫዎችን ያወጣሉ ብለዋል። የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችም ሆኑ አጋር ድርጅቶች በሕገ መንግሥቱ አማካኝነት ሲያሸንፉ መንግሥት እየመሰረቱ ህዝቦችን እያስተዳደሩ እንደቆዩም ተናግረዋል።
ከሕገ ወጥ ንግድ ጋር በተያያዘም ወርቅ ወደ ሱዳን ብቻ ሳይሆን በመሐል ሀገር አቋርጦ ወደ ተለያዩ አገሮች ይወጣል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሕገ ወጥ ተግባሩን ለመከላከል የግንዛቤ መፍጠር ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣
ኮንትሮባንድና ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን በጋራ ለመከላከል ሲሰራ መቆየቱን እና ትልቅ ውጤት መገኘቱንም ተናግረዋል።
እንደ አቶ አሻድሌ ገለፃ፤ የሚነሱ የሰላምና የልማት ጥያቄዎችን መንግሥት ከህዝቡ ጋር በመሰለፍ የሚፈታበት ዕድል አለ። ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በሰለጠነ አግባብ መፍታት የሚቻልበትን ባህል ማዳበር ይገባል። ለአገር ልማትና ሰላም የሚጠቅም አመለካከትና አስተሳሰብ በመያዝም የታየውን ተስፋ ሰጪ ለውጥ ማስቀጠል ይገባናል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2012
ዘላለም ግዛው