አዲስ አበባ፡-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የ2019 የዓለም የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን ተከትሎ በተለያዩ ከተሞች የደስታ መግለጫ ሰልፎች ተካሄደዋል።
ሰልፎቹ በኦሮሚያ ክልል፣ በአዳማ፣ በዱከም፣ ገላን፣ ሻሸመኔ፣ አምቦ፣ ወሊሶ፣ ቢሾፍቱ፣ ለገጣፎ፣ ለገዳዲ፣ ሰበታ፣ ሱሉልታ፣ ባሌ ሮቤ፣ ጅማ፣ መቱ፣ ኢሉ አባቦሩ፣ በደሌ፣ ባቱ፣ ጭሮ፣ አርሲ፣ ነቀምት፣ ጉጂ ዞን፣ ቦረና ዞን፣ እና ሌሎች በርካታ ከተሞች ተደርገዋል። የከተሞቹ ነዋሪዎቹ በነቂስ ወደ አደባባይ በመውጣትም ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የ2019 የሰላም ኖቢል ተሸላሚ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታና የእንኳን ደስ አልዎ መልዕክት በመግለጽ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄደዋል።
የሰልፉ ተሳታፊዎችም፤ በሰልፎቹ ላይ “የኖቤል የሰላም ሽልማት የመደመር ፍልስፍና ውጤት እና አሸናፊ ሐሳብ ዓለም አቀፍ ሽልማትን ያመጣል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ ሰላምና ብልፅግና እንዲረጋገጥ የሚያደርጉትን ጥረት እንደግፋለን ፤ የመደመር ፍልስፍና ኢትዮጵያንና የአፍሪካ ቀንድን ሰላም የሚያረጋግጥ ነው”። የሚሉ መፈክሮችን በመያዝ ወጥተዋል። በሽልማቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው በመግለፅ ለሰላም ሁሉም መትጋት እንዳለበት ያሳያል ብለዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አሰግድ ጌታቸው ለሰልፈኞቹ ባደረጉት ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት በስደት ላይ የነበሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመልሰው በሐሳብ እንዲሞግቱ ያደረጉ ቆራጥ መሪ መሆናቸውን ገልፀዋል። በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላምና ወንድማማችነትን በማስፈን የለውጥ ኃይል በመሆናቸው ለሽልማት እንዳበቃቸው ተናግረዋል።
የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መኪዩ መሐማድ በሳሙት ንግግር “ ለዶክተር አብይ የተሰጠው የኖቤል ሽልማት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው” ብለዋል። ሽልማቱ በከተማውም ሆነ በአገሪቱ እኩልነት በማሰፍን ለህዝቦች ተጠቃሚነት ሁሉም ጠንክሮ እንዲሠራ ብርታት እንደሚሆን አመልክተዋል።
በጅማው ሰልፍ ላይ የተገኙት አቶ ሌንጮ ባቲ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያመጡትን ስኬት በማንሳት፥ ከዚህ በኋላ መወቃቀስ አቁመን አገራችንን ወደ ፊት ለማራመድ እንነሳ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአምቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ቱፋ አብዲ “አሁን ያገኘነውን ሰላም ብናስቀጥል የበለጠ ሽልማት እናገኛለን፤ ስለዚህ አንድነታችንን ካጠናክረን ከማሸነፍ የሚያግደን የለም “ብለዋል።
እንዲሁም ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባገኙት የኖቤል የሰላም ሽልማት የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ በድሬዳዋ ከተማ፣ በሐረሪና በሱማሌ ክልሎች የጅግጅጋ ነዋሪዎች እና የአካባቢው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰማቸውን ደስታ በድጋፍ ሰልፎችም ገልፀዋል። ከጎናቸው እንደሚቆሙ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በሰልፉ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞችንና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
በተያያዘ ዜናም ትናንት የካቢኔ አባላት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ተገኝተው ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት በማግኘታቸው ደስታቸውን ገልፀዋል። ለአመራሩ እንዲሁም ለተገኘው ስኬት ያላቸውን አድናቆት ለመግለጽ የወርቅ ሐብል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያበረከቱ ሲሆን “እውነት ፍቅር ያሸንፋል” የሚል ጽሑፍ ተቀርፆበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ለዚህ ታላቅ ሽልማት በመብቃታቸው የተለያዩ የዓለም አገራት መንግሥታት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችን ጨምሮ የተለያዩ ወገኖች የእንኳን ደስ ያልዎት መልዕክት አስተላልፈውላቸዋል።
የኖቤል የሰላም ሽልማትን የሚያሸንፉ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች 900 ሺ ዶላር የሚሰጣቸው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሰላም እና ለዓለም አቀፍ ትብብር ላደረጉት ጥረት በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለዓመታት የዘለቀውን የድንበር የይገባኛል ውዝግብ በሰላም እንዲፈታ ተነሳሽነትን በመውሰዳቸው የ2019 የኖብል የሰላም ተሸላሚ ሆነዋል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህምድ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊነት ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ኢትዮጵያ ላይ ያለውንም ተስፋ ያመላከተ መሆኑን አመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማትን በማሸነፍ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ ሰላም፣ ይቅርታና ፍቅርን ከማቀንቀን አቋርጠው እንደማያውቁም አንስተዋል። በአገር ውስጥ የነበረውን አስፈሪ የፖለቲካ ፍጥጫ በማርገብ፣ በውጭ አገር የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገር እንዲገቡ በማድረግ፣ ያለፈውን ታሪክ ዕሴቶች አስጠብቀን እንድንጓዝ ማድረጋቸውንም አውስተዋል። ስህተቶችንም አርመን፣ አዳዲስ ዕሴቶችን በመጨመር የምንሄድበትን አካሄድ በመንደፍ፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረውንና ሁለት አስርተ ዓመታት ያስቆጠረውን ውጥረት በሠላም መፍታታቸውንም አስረድተዋል።
በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ትብብርን በማበረታታት፣ በጎረቤት አገራት መካከል የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚቻላቸውን ሁሉ ማድረጋቸውን ገልፀዋል። ከሁሉም መአዘን እያስተጋባ ያለው የደስታ ስሜት ኢትዮጵያዊያን አንገታችንን በኩራት ከፍ እንድናደርግ የሚጋብዘን እና ልንኮራበት የሚገባ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነንና ተባብረን ሰርተን ያልተሳካልን ጊዜ የለም ያሉት ፕሬዚዳንቷ ፉክክራችንን ርዕስ በርዕስ ማድረጋችንን ትተን ከዓለም ጋር ካደረግነው ማሸነፍ እንደምንችል ታሪክ በተደጋጋሚ ነግሮናል ነው ያሉት።
አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ነፃ እንዲወጡ አብረን በመታገል እንደተሳካልን በመግለጽ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲመሰረት ኢትዮጵያ የበኩሏን ማድረጓንም አስታውሰዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2012